አሜሪካዊያን በክሪፕቶከረንሲ አማካኝነት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዘረፋቸው ተገለጸ
ገንዘብ መንታፊዎቹ ማህበራዊ የትስስር ገጾችን ተጠቅመው ዘረፋውን ፈጽመዋል ተብሏል
ኤፍቢአይ አሜሪካዊያን ራሳቸውን ከመንታፊዎች እንዲጠብቁ ሲል አሳስቧል
አሜሪካዊያን በክሪፕቶከረንሲ አማካኝነት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዘረፋቸው ተገለጸ፡፡
የአሜሪካው ወንጀል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ይፋ እንዳደረገው ከሆነ አሜሪካዊያን ባለፈው ዓመት 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በበይነ መረብ አማካኝነት ገንዘባቸውን ተዘርፈዋል፡፡
ምናባዊ ገንዘብ ወይም ክሊፕቶከረንሲን እንደ ምክንያት በመጠቀም ተፈጽሟል የተባለው ይህ ዘረፋ ከዓመት ዓመት እየጨመረ እንደመጣም ተገልጿል፡፡
በ2023 ዓመት የተፈጸመው ዘረፋ ከ2022 ጋር ሲነጻጸርም በ45 በመቶ እንደጨመረ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዪ (ቪኦኤ) ዘግቧል፡፡
በአጠቃላይ በዚሁ ዓመት 70 ሺህ አሜሪካዊያ ገንዘባችንን ተዘረፍን በሚል ለኤፍቢአይ አመልክተዋል የተባለ ሲሆን ቢትኮይንን በመጠቀም ዘረፋ የሚፈጽሙት ትልቁን ቁጥር ይይዛሉም ተብሏል፡፡
አብዛኛው ዘረፋ የሚከናወነው በክሊፕቶከረንሲ ላይ ኢንቨስት አድርጉ በሚል ሰበብ እንደሆነ የገለጸው የኤፍቢአይ ሪፖርት በዚህ መስክ የ3 ነጥብ9 ቢሊዮን ዶላር ዝርፊያ ተፈጽሟል፡፡
በኤፍቢአይ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ዳይሬክተር የሆኑት ሚካኤል ኖርድዎል እንዳሉት አብዛኞቹ ዘረፋዎች የሚካሄዱት ማህበራዊ ሚዲያዎችን እና የፍቅር ጓደኝት መፈለጊያ መተግበሪያዎች አማካኝነት የተፈጸሙ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የዝርፊያ ወንጀሎቹ የሚፈጸሙት መጀመሪያ ላይ ጓደኝነት ወይም ወዳጅነት የፈለጉ በመምሰል ከቀረቡ በኋላ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በመካከላቸው እምነትን ከፈጠሩ በኋላ ሀሰተኛ ሊንኮችን በመላክ እንዲጫኑ አልያም እንዲከፍቱ በማድረግ የገንዘብ ምንተፋውን ይጀምራሉም ብለዋል፡፡
ዕምነት ከፈጠሩ በኋላም የተወሰኑት ያጠመዱት ሰው አነስተኛ ገንዘብ በክሊፕቶከረንሲ አማካኝነት ገንዘብ እንዲያገኝ ማድረግ ካስጀመሩ እና ይህንን ለጥት ወራት ካደረጉ በኋላ ዘረፋውን እንደሚፈጽሙም ተናግረዋል፡፡
ሁሉም አሜሪካዊያን ከመላው ዓለም የገንዘብ መንታፊዎች ዋና ኢላማ መሆኑን አውቆ ሊጠነቀቅ እንደሚገባ እና በአካል አግኝተውት የማያውቁትን ሰው ከማመን እንዲቆጠቡም ኤፍቢአይ አሳስቧል፡፡