61 በመቶ አሜሪካውያን ሀገራቸው ኢራቅን መውረሩ ስህተት እንደሆነ ያምናሉ ሲል አንድ ጥናት አመልክቷል
አብዛኞቹ አሜሪካዊያን የኢራቅ ወረራ ስህተት እንደሆነ ይምናሉ ተባለ።
ከ20 ዓመት በፊት የወቅቱ የኢራቅ ፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴን ጅምላ ጨራሽ የጦር መሳሪያ አላቸው በሚል የአሜሪካ እና አጋሮቿ ጦር ወደ ባግዳድ ገብቷል።
የዋሽንግተን እና አጋሮቿ ጦርም ባደረገው ወረራ በፕሬዝዳንት ሳዳም ሁሴን የሚመራውን መንግሥት ከስልጣን ከማውረዱ በተጨማሪ አይነተ ብዙ ውድመቶች በኢራቃዊያን ላይ ተከስቷል።
አክሲዮስ የተሰኘው የህዝብ ጥናት ተቋም ባወጣው መረጃ አብዛኛው አሜሪካዊያን የሀገራቸው ጦር ወደ ኢራቅ መግባቱ ስህተት ነው ብለው ያምናሉ።
በፈረንጆቹ 2003 ላይ የአሜሪካ ጦር ወደ ኢራቅ መግባቱን የተቃወሙ አሜሪካዊያን 26 በመቶ ብቻ እንደነበሩ ተገልጿል።
ይሁንና ወረራው ከተፈጸመ 20 ዓመት በኋላ የአሜሪካ ጦር ወደ ኢራቅ መግባቱ ስህተት ነው የሚሉ አሜሪካዊያን ቁጥር 61 በመቶ መድረሱን ይሄው ተቋም ያስጠናው ጥናት ያስረዳል።
በወቅቱ 83 በመቶ የሚሆኑ የሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊዎች የአሜሪካ ጦር ወደ ኢራቅ እንዲገባ ፈልገው ነበርም ተብሏል።
አሁን ላይ ደግሞ 58 በመቶ ሪፐብሊካኖች አሁንም የሀገራቸው ጦር ኢራቅን መውረሩ ትክክል እንደሆነ እንደሚያምኑ ተገልጿል።
በጥናቱ ከተሳተፉ ከአንድ ሺህ በላይ አሜሪካዊያን መካከል 64 በመቶዎቹ አሁንም የዋሽንግተን ጦር በኢራቅ መኖሩ ትክክል እንዳልሆነ ያምናሉም ተብሏል።
እንዲሁም 54 በመቶዎቹ አሜሪካዊያን ሀገራቸው ከዓለም አቀፍ ጉዳዮች ይልቅ ሀገር ውስጥ ደህንነት ትኩረት እንድትሰጥ ፍላጎት እንዳላቸው ጥናቱ ያስረዳል።
በፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ መሪነት የተፈጸመው የኢራቅ ወረራ ከ210 ሺህ በላይ ኢራቃዊያንን ህይወት መቅጠፉ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም በኢራቅ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት አለመመስረቱን ተከትሎ በተደጋጋሚ የሽብር ጥቃቶችን እየደረሰባትም ይገኛል።