ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ስልጣን ከያዙ ወዲህ በታጣቂ ቡድኑ ላይ አየር ድብዳባ እንዲፈጸም ሲያዙ ይህ ለ2ኛ ጊዜ ነው
አሜሪካ በኢራቅ እና በሶሪያ ድንበሮች አካባቢ ላይ የአየር ድበደባ መፈጸሟ ተሰምቷል።
የአየር ድበደባው በኢራቅ እና በሶሪያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እና በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው ሚሊሻዎችን ኢላማ ያደረገ መሆኑንም ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ፔንታገን ገለጻ የእሁዱ የአየር ድበዳባ በሁለቱ ሀገራት ድንበር አካባቢ የሚንቀሳቀሰው የሚልሻው ቡድን ዘመቻዎች መምሪያ እና የመሳሪያ ማከማቻን ኢላማ ያደረገ ነው።
ሀገሪቱ የአየር ድብደባውን የፈጸመችው በታጣቂ ቡድኑ አሜሪካ ጦር ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ለፈጸመው ጥቃት አጸፋ እርምጃ ነው።
ፔንታጎን የአየር ድብደባውን ተከትሎ ስለደረሰው ጉዳት መረጃ ያልሰጠ ሲሆን፤ ሁኔታውን የሚከታተሉ ቡድኖች ግን በሶሪያ 5 የታጣቂ ቡድን አባላት መሞታቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በርከት ያሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት መቁሰላቸውን መቀመጫውን ብሪታንያ ያደረገው እና የሶሪያ ሰብአዊ መብቶች ሁንታውን የሚከታተለው ቡድን ገልጿል።
የሶሪያ መንግስት የዜና አገልግሎት በበኩሉ በአየር ድብደባው የአንድ ህጻን ልጅ ህይወት ማለፉን እና ሌሎች 3 ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አሜሪካን መምራት ከጀመሩ ወዲህ በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት ታጣቂ ቡድን ላይ አየር ድብዳባ እንዲፈጸም ሲያዙ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
መቀመጫውን ኢራቅ ያደረገው የአሜሪካ ጦር ከቅርብ ወራት ወዲህ በርከት ያሉ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃት ሙከራዎች የተደረጉበት ሲሆን፤ ኢራን በበኩሏ “እጄ የለበትም” ስትል አስተባብላለች።