ቡሽ አሜሪካ እ.ኤ.አ በ 2003 ወታደሮቿን ወደ ኢራቅ እንድትልክ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ሩሲያ ``ዩክሬንን ወረረች`` በማለት ፋንታ የኢራቅ ስም ማንሳታቸው እያነጋገረ ነው፡፡
ጉዳዩን አነጋጋሪ ያደረገው ደግሞ እ.አ.አ በ 2003 አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ኢራቅ ስትልክ ትዕዛዙን የሰጡት ቡሽ መሆናቸው ነው፡፡
የ75 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት በአሜሪካ ዳላስ በተዘጋጀ የዴሞክራሲ ውይይት ላይ ፕሬዝዳንት ፑቲንን ለመተቸት`` ሩሲያ ዩክሬንን ወረረች`` በማለት ፋንታ የኢራቅ ወረራ ብለው ነበር፡፡
ቡሽ ከወቅታዊው የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ጋር በተያያዘ፤ የሩሲያውን ፕሬዝዳንት እያወገዙ ሳለ ነው ስህተቱን የፈጸሙት፡፡ በዳላስ ባደረጉት ንግግር የፈጸሙትን ስህተት ወዲያው ቢያርሙትም መነጋገሪያነቱ ግን ቀጥሏል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ``ምክንያታዊ ያልሆነና ጭካኔ የተሞላበት አንድ ሰው የጀመረው የኢራቅ ወረራ`` ካሉ በኋላ የመድረኩ ተሳታፊዎች ሲስቁ ወዲያው ዩክሬን በሚል አስተካክለዋል፡፡ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የኢራቅን ስም ከጠሩ በኋላ ዕድሜያቸው 75 ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተከሰተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አሜሪካ በኢራቅ አድርጋው በነበረው ጦርነት ከፍተኛ ትችት የሚቀርብባቸው ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የኢራቅን ስም ካነሱ በኋላ የ 2003 የጦርነት ትዝታዎች እንደተቀሰቀሱ ነው፡፡
ጦርነቱ በ 2003 ከመጀመሩ አስቀድሞ የቀድሞው የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር ሀገራቸው ለአሜሪካ ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸው እንደነበር ከአንድ ማስታወሻ ላይ መገኘቱ ይታወሳል፡፡