ከዋናው የድምጽ መስጫ ቀን በፊት እስካሁን 94 ሚሊዮን ሰዎች ድምጻቸውን መስጠታቸው ተገልጿል
አሜሪካውያን ቀጣዩን ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ነገ የመጨረሻ ድምጽ ይሰጣሉ
በአሜሪካ የምርጫ ታሪክ እድሜ ጠገብ የሆኑት ሁለቱ አዛውንት እጩዎች ዛሬ የመጨረሻ ቅስቀሳቸውን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ድምጽ ያላቸውእና በተለምዶ የምርጫውን ውጤት የሚወስኑት የአሜሪካ ግዛቶች ደግሞ የአዛውንቶቹ ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን እንዲሁም የምክትሎቻቸው የምረጡን ዉትወታ መዳረሻ ናቸው፡፡
ምርጫው ከመጀመሩ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍሎሪዳ ፣ ጆርጂያ ፣ ሎዋ እና በማሳረጊያቸውም ሚቺጋንን ይጎበኛሉ፡፡ እነዚህ ግዛቶች በ2016 ምርጫ ፕሬዝዳንቱ ያሸነፉባቸው ቢሆኑም አሁን ግን በስጋት የሚመለከቷቸው ናቸው፡፡
ትራምፕ በሚቺጋን ቅስቀሳ ከመጀመራቸው በፊት በአካባቢው ብርዳማ አየር ሲቀልዱ
የዲሞክራቶቹ እጩ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደግሞ የመጨረሻ ቅስቀሳቸውን 20 ድምጽ ባለው በፔንሲልቫኒያ 4 ስፍራዎች ያደርጋሉ፡፡
ባይደን በአትለንታ ጆርጂያ ከሳምንት በፊት ቅስቀሳ ሲያደርጉ
በመጨረሻዋ የውጥረት እለት ለምክትልነት ያጯቸው ካማላ ሃሪስ ደግሞ ጆርጂያን እና ሰሜን ካሮላይናን ይይዙላቸዋል፡፡
ካማላ ሃሪስ በሰሜን ካሮላይና ትናንት ጥቅምት 22/2013 ዓ.ም
እስካሁን የተሰጠ ድምጽ
በድምጽ መስጫው ቀን የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስ እና በርካታ ህዝብ እንዲመርጥ ለማበረታታት በሚል ከዋናው የድምጽ መስጫ ቀን በፊት በአሜሪካ ድምጽ መስጠት የሚቻል ሲሆን እስካሁን 94 ሚሊዮን ሰዎች ድምጻቸውን መስጠታቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህም በ2016 ከምርጫው ቀን በፊት ከተሰጠው ድምጽ ጋር ሲነጻጸር በ68 በመቶ ይበልጣል፡፡ ይህም በዘንድሮው ምርጫ በሀገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ እንደሚመርጥ አመላካች ነው፡፡
የመጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳ ሩጫ
የትራምፕ እና የባይደን ዋነኛ የምርጫ ቅስቀሳ ነጥብ የኮሮና ቫይረስ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ምንም እንኳን ኮሮናቫይረስ ከ230 ሺህ በላይ አሜሪካውያንን ህይወት ቢነጥቅም ፣ ትራምፕ የአሜሪካ ኢኮኖሚ ያለምንም ገደብ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ የቅስቀሳቸው ትኩረት ነው፡፡ በፕሬዝዳንቱ የኮሮና አያያዝ ላይ ከፍተኛ ትችት የሚሰነዝሩት ተቀናቃኛቸው ባይደን በበኩላቸው ወረርሽኙን ለመግታት ጠንካራ እርምጃዎችን እንደሚወስዱ በተደጋጋሚ ገልጸዋል፡፡
የልዕለ ሀያሏ ሀገር ቀጣይ መሪ ለመሆን ፣ ሁለቱ ተቀናቃኞች ከሀገሪቱ አጠቃላይ 538 ድምጽ (ኤሌክቶራል ኮሌጅ) 270 እና ከዚያ በላይ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህ ድምጾች በተለያዩ መስፈርቶች ለሀገሪቱ ግዛቶች በተለያየ መጠን የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም በየግዛቶቹ (በተለይም ከፍተኛ ድምጽ ባላቸው) ውጤት ማስመዝገብ እንጂ በ2016ቱ ምርጫ እንደታየው የአብዛኛውን ህዝብ ድምጽ ማግኘት ብቻ ለአሸናፊነት አያበቃም፡፡ በ2016 ምርጫ በአጠቃላይ የመራጮች ቁጥር ሂላሪ ክሊንተንን የመረጡ ቢበልጡም የመጨረሻው ውጤት ግን ኋይት ሀውስ መግባት እንዳላስቻላቸው ይታወሳል፡፡ ለዚህም ነው ትራምፕ እና ባይደን ከፍተኛ ድምጽ ባላቸው ግዛቶች ላይ እግራቸውን ያበዙት፡፡
የቅድመ ምርጫ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የመጨረሻውን ውጤት የመወሰን አቅም ካላቸው ግዛቶች መካከል በፍሎሪዳ ፣ ሰሜን ካሮላይና ፣ ጆርጂያ ፣ ፔንሲልቫኒያ እና ሚቺጋን ሁለቱ ተፋላሚዎች ተቀራራቢ ድምጽ ያላቸው ሲሆን ከተቀሩት ደግሞ ከአዮዋ እና ኦሀዮ በስጠር በሌሎቹ ባይደን በትንሽ ልዩነት ይመራሉ፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን ባይደን የ8.6 በመቶ ብልጫ እንዳላቸው ጥናቶች ያመለክታሉ ሲል ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ውጤቱ መች ይታወቃል
የምርጫው ውጤት ከቀደሙት ጊዜያት ዘግይቶ ሊወጣ እንደሚችል የሲኤንኤን እና የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡ እንደወትሮው ድምጽ በተሰጠ ማግስት አሸናፊውን መለየት ዘንድሮ ብዙም አይታሰብም ፤ ምናልባትም ውጤቱን ለማወቅ ቀናትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ኮሮና ቫይረስ ሁኔታዎችን ማወሳሰቡ ሲሆን በፖስታ የተሰጡ ድምጾችን ቆጥሮ የመጨረሻውን ውጤት ለማሳወቅ ጊዜ ይፈልጋል፡፡