ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሆስፒታል ወጥተው ኋይት ሀውስ ተመልሰዋል
"ኮቪድን አትፍሩት ፤ እንዲቆጣጠራችሁ አትፍቀዱለት"-ፕሬዝዳንት ትራምፕ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ህክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል በመውጣት ወደ ኋይት ሀውስ ተመልሰዋል፡፡
ይሁንና ፕሬዝዳንቱ ኋይት ሀውስ እንደገቡ ባደረጉት ንግግር አሜሪካውያን ኮቪድ-19ን እንዳይፈሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ቫይረሱ በአሜሪካ ብቻ ከ 210,000 የሚጠጉ ሰዎችን ለሞት ዳርጎ እርሳቸውም 4 ቀናትን በሆስፒታል እንዲያሳልፉ ምክንያት ሆኖ ሳለ ህዝቡ ቫይረሱን እንዳይፈራ መናገራቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡
የአፍና አፍንጫ ማስካቸውን ማውለቃቸውም በፕሬዝዳንቱ ላይ አዲስ የትችት በር ከፍቷል፡፡
"ኮቪድን አትፍሩት ፤ እንዲቆጣጠራችሁ አትፍቀዱለት" ሲሉ ከዋልተር ሪድ ህክምና ማዕከል ወጥተው ወደ ነጩ ቤተ-መንግሥት ሲመለሱ በለቀቁት ቪዲዮ ተናግረዋል፡፡ "እኔ ተሸሎኛል ፣ ምናልባት በሽታ የመከላከል አቅሜ ነው - አላውቅም" ሲሉም በንግግራቸው አንስተዋል፡፡
አሁንም በሽታውን በማጣጣል ያደረጉት ንግግር የህክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ብዙዎችን እንዳስገረመ እና እንዳስደነገጠም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በናሽቪል በሚገኘው በቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ማዕከል የመከላከያ ህክምና እና ተላላፊ በሽታዎች ፕሮፌሰር የሆኑት ዊሊያም ሻፍነር “ፕሬዝዳንቱ ኮቪድ መፈራት የለበትም ሲሉ በጣም ተደንቄያለሁ” ብለዋል፡፡ “ይህ በቀን ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን የሚገድል ፣ ኢኮኖሚን የሚያደናቅፍ ፣ ሰዎችን ከስራ ያፈናቀለ በሽታ ነው ፡፡ ይህ መከበርም ሆነ መፈራት ያለበት ቫይረስ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
በዶክተሮች ሰራዊት ታክመው በሙከራ ላይ በሚገኙ መድኃኒቶች ህክምና ያገኙት ትራምፕ በዓለም ዙሪያ ከ 1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የገደለውን እና ሀገራቸውን ከዓለም በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃውን በሽታውን በተደጋጋሚ ሲያጣጥሉ ቆይተዋል፡፡
እ.ኤ.አ የፊታችን ህዳር 3 በሚካሄደው ምርጫ ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን ጋር በድጋሚ ለመመረጥ የሚወዳደሩት የሪፐብሊካኑ ተወካይ ፕሬዝዳንት ባለፈው አርብ ዕለት ነበር በበሽታው ተይዘው ሆስፒታል የገቡት፡፡
በቅርቡ ወደ ምርጫ ቅስቀሳቸው እንደሚመለሱም ፕሬዝዳንቱ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ወትሮውንም የፕሬዝዳንቱን የቫይረሱን አያያዝ የሚተቹት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ሴናተሮችም ትችታቸውን ቀጥለዋል፡፡
ከፕሬዝዳንቱ ጋር በቀጣዩ ምርጫ የሚወዳደሩት ጆ ባይደን ፕሬዝዳንቱ ማስካቸውን ሲያወልቁ እና እርሳቸው ደግሞ ማስክ እያደረጉ የሚያሳይ ፎቶ ጎን ለጎን አድርገው “ማስኮች አስፈላጊ ናቸው። ህይወትን ይታደጋሉ” ከሚል ጽሁፍ ጋር በትዊትር ገጻቸው በመለጠፍ ለፕሬዝዳንቱ ፈጣን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ጉዳይ ለቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አንዱ ዋነኛ መከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡