ትራምፕ እና ባይደን ትናንት ምሽት ፊት ለፊት ተከራከሩ
ወቅታዊውን የኮሮና ወረርሽኝ እና ዘረኝነትን ጨምሮ በተለያዩ ነጥቦች ዙሪያ ነው ክርክራቸውን ያደረጉት
የሁለቱ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ክርክር በስድብ እና ጭቅጭቅ የተሞላ ነበር
ትራምፕ እና ባይደን ትናንት ምሽት ፊት ለፊት ተከራከሩ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ተፎካካሪዎቻቸው ጆ ባይደን በዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ እጅግ በጣም ጭቅጭቅ የበዛበት እና ትህትና የጎደለው የኋይት ሀውስ ክርክር አድርገዋል፡፡
በ ክሌቭላንድ ፣ ኦሃዮ በተካሄደው የ90 ደቂቃው መድረክ ላይ ቁጣ በተሞላበት ክርክራቸው በኮሮና ወረርሽኝ ፣ በዘረኝነት ፣ በኢኮኖሚ እና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ነው የተከራከሩት፡፡
ዴሞክራቱ ባይደን ፕሬዚዳንቱን “ቀልደኛ ተዋናይ” ያሏቸው ሲሆን በንግግራቸው ጣልቃ እየገቡ ሲያስቸግሯቸው “ዝም በል” ሲሉም ተናግረዋቸዋል፡፡ ትራምፕ በበኩላቸው የተፎካካሪያቸውን ልጅ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት አንስተዋል፡፡
አስተያየቶች እንደሚጠቁሙት ባይደን ትራምፕን በ አንድ አሃዝ ጠባብ ልዩነት እየመሩ ነው፡፡
ይሁንና ለምርጫው 35 ቀናት በሚቀሩበት በአሁኑ ወቅት ከበርካታ ግዛቶች የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች የጠበቀ ውድድር መኖሩን ያሳያሉ፡፡
በምሽቱ መድረክ የ15 ደቂቃ ክፍል የተደረገው ክርክር በ6 ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነዚህም- የእጩዎቹ ስራዎች ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፣ ወረርሽኙ ፣ የዘረኝነት ጉዳይ ፣ የምርጫ ታማኝነት እና ኢኮኖሚ ናቸው ቢቢሲ እንደዘገበው፡፡
በስድብ በተሞላው የአዛውንቶቹ ክርክር የ 77 ዓመቱ ባይደን የ74 ዓመቱን ፕሬዝዳንት ትራምፕን “በአሜሪካ ታሪክ እስካሁን ታይቶ የማያውቅ አሳፋሪ ፕሬዝዳንት ነዎት” ብለዋል፡፡
ዘረኝነትን በተመለከተ ባደረጉት ክርክር ፕሬዚዳንቱ የነጭ የበላይነትን የሚያራምዱ ሰዎችን ለማውገዝ ዝግጁ ስለመሆን አለመሆናቸው ከአከራካሪው ጥያቄ ተነስቶላቸዋል፡፡
በመጀመሪያ አወግዛለሁ ብለው የነበሩት ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን ጽንፈኛ የቀኝ አክራሪ “የኩሩ ወንዶች ቡድን” (Proud Boys group)ን በስም ጠቅሰው እንዲያወግዙ ሲጠየቁ ግን አድበስብሰው ወደጎን ትተውታል፡፡
ቀደም ብለው ባይደን “ይህ ሁሉን እንደ ውሻ ጩኸት የዘረኝነት ጥላቻን ፣ የዘረኝነት ክፍፍልን ለማምጣት የሞከረ ፕሬዝዳንት ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ በበኩላቸው ባይደን ሕግ የማስከበር ፍላጎት እንደሌላቸው “ሕግ ማስከበር የሚለውን ቃል እንኳን መናገር አትችልም ምክንያቱም እነዚህን ቃላት ከተናገርክ ሁሉንም አክራሪ የግራ ደጋፊዎችህን ታጣለህ” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል፡፡
ከ200 ሺ በላይ አሜሪካውያንን ህይወት የነጠቀው የኮሮና ቫይረስ ሌላው የተከራከሩበት ነጥብ ሲሆን በዚህ ረገድ ባይደን የትራምፕን አስተዳደር አንቋሸው ገልጸዋል፡፡
የቫይረሱ ስርጭት የትራምፕ ማንነት መገለጫ እንደሆነ ነው “አንተ አንተን ስለሆንክ ቫይረሱ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል” በማለት ጆ ባይደን የገለጹት፡፡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ግን በተለመደ ማድበስበሻ ክሱን አልተቀበሉትም፡፡
በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ሁለቱ እጩዎች ክርክር ያደረጉ ቢሆንም ክርክሩ ከፍሬ ነገሩ ይልቅ በስድብ እና በጭቅጭቅ የተሞላ በመሆኑ በብዙዎች ዘንድ አልተወደደም፡፡
የምሽቱ ክርክር “ለህዝቡ ምንም ትምህርት የማይሰጥ እና አራት ዓመት ቢሰጣቸው ምን ሊሰሩ እንደሚችሉ እንኳን ፈንጭ ያልሰጠ” በሚል በብዙዎች እንደተተቸም ተዘግቧል፡፡
ሁለቱ ተቀናቃኞች እስከምርጫው ዕለት ድረስ በቀጣይነት ሶስት መሰል ክርክሮችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡