የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ወታደሮች በአማራ ክልል ባለው ውጊያ እየተሳተፉ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገለጸ
ተቋሙ የባህር ሀይል አባላቱ በ"ጽንፈኞች" ላይ እርምጃ እየወሰዱ ነው ብሏል
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና "ፋኖ" ታጣቂዎች መካከል ግጭት ከተጀመረ አንድ ዓመት ሞልቶታል
የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ወታደሮች በአማራ ክልል ባለው ውጊያ እየተሳተፉ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገለጸ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ "የኢትዮጵያ ባህር ሀይል ማሪን ኮማንዶ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተሰማርቷል" ብሏል።
ተቋሙ የባህር ሀይል ዋና አዛዥ ተወካይ ሬር አድሚራል ናስር አባዲጋን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የባህር ሀይል ማሪን ኮማንዶዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ባሉ ወረዳዎች ግዳጃቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ማሪን ኮማንዶ በመርከብ ላይ በባህር ከሚሰጠው ተልዕኮ በተጨማሪ በማንኛውም ጊዜ ግዳጁን የሚወጣ ሀይል መሆኑንም ሬር አድሚራል ናስር አባድጋ መናገራቸውን የሀገር መከላከያ ስራዊት ገልጿል።
ማሪን ኮማንዶ ከአማራ ክልል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በወሰዳቸው እርምጃዎች የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱንም በዚሁ ዘገባ ላይ ተጠቅሷል።
የፌደራል መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን "መልሼ አደራጃለሁ" የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ ነበር በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተው።
ግጭቱ በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የ"ፋኖ" ታጣቂዎች መካከል የተካሄደ ሲሆን ግጭቱ ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
ከሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የታወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት የተራዘመ ሲሆን ይህ አዋጅ ሊጠናቀቅ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል።
የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲየስ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በአማራ ክልል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ከ700 በላይ ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ መናገራቸው ይታወሳል።
በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና የፋኖ ታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ ንጹሀን ዜጎች ከጥቃት እየተጠበቁ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ተመድን ጨምሮ በርካታ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርት ላይ ጠቅሰዋል።
ለአብነትም በባህር ዳር፣ መራዊ፣ ማጀቴ እና ሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ንጹሀንን ሆን ብለው እንደገደሉ ተቋማቱ በሪፖርቶቻቸው ላይ የገለጹ ሲሆን የፌደራል መንግሥት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የቀረቡ ቅሬታዎችን ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።