በሰኔ 15ቱ ክስተት ከተከሰሱ ተከሳሾች መካካል የተወሰኑት ክሳቸው ተነበበላቸው
በአማራ ክልል ሰኔ 15፣ 2011 ዓ. ም በተከሰተዉ የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ በእነ ሻምበል መማር ጌትነት መዝገብ የተከሰሱት 55 ተከሳሾች የክስ ምክንያት ዛሬ መነበብ መጀመሩን የአማራ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
የተከሳሾቹ ጉዳይ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡
ችሎቱ እስከ ምሳ ሰዓት የተወሰኑ ተከሳሾችን ክስ በዝርዝር አንብቦ አሰምቷል፤ ቀሪ የክስ ዝርዝሮችን ዛሬ ከምሳ በኋላ ለማሰማትም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በዚህ የክስ መዝገብ ውስጥ 55 ተከሳሾች ተዘርዝረዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ አምስቱ ጉዳያቸው በሌሉበት የሚታይ ነው፡፡
በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ሰኔ 15፣ 2011 ዓ. ም በተፈጸመው ግድያ የክልlu ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን፣ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪያቸው አቶ እዘዝ ዋሴ፣ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደ ህይወታቸው ማለፉ ይታወቃል፡፡ የዚህ ግድያ ወንጀል አካል ነው በተባለውና በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በአዲስ አበባ በተፈጸመው ግድያ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ምንጭ፡ አብመድ