ኢትዮጵያ በሴካፋ ውድድር አትሳተፍም ተባለ
ኢትዮጵያ በመጪው ቅዳሜ ኡጋንዳ በሚጀመረው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ውድድር /ሴካፋ/ እንደማትሳተፍ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከሕዳር 27 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2012 ዓ.ም በዩጋንዳ በሚካሄደው ውድድር እንድትሳተፍ የምድብ ድልድል ውስጥ መካተቷ ይታወቃል።
ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከውድድሩ ከሚገኘው ጥቅምና ከሚወጣበት ወጪ አንጻር መሳተፉ አስፈላጊ እንዳልሆነ ይፋ አድርጓል፡፡
የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ፌዴሬሽኑ ያለውን ውስን በጀት ለሴካፋ ውድድር ማዋሉ ጠቃሚ እንዳልሆነ ያምናል።
አንድ ውድድር የሚለካው በተሳትፎ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጥቅሞች ተገምግመው ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ እንደማትሳተፍ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፈደሬሽን (ካፍ) አካል የሆነው ቀዳሚው የአፍሪካ ቀጣናዊ ውድድር -ሴካፋ፣ የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የሚሳተፉበት ነው፡፡
ምንጭ፦ ኢዜአ