የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ወደ ባንክ ሂሳብ ገቢ ማድረግ የሚያስችል ኤቲኤም ማሽን ከሰሞኑ ስራ ላይ አዋለ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ገቢ ማድረግና የውጭ ምንዛሬ መመንዘር የሚያስችል የኤቲኤም (ATM) ማሽን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን አስታወቀ።
አዲሱ ማሽን ቀደም ሲል አገልግሎት ላይ ከዋለው የገንዘብ መክፈያ የኤቲኤም /ATM/ ማሽን ከሚሰጠው ገንዘብ የመክፈል አገልግሎት በተጨማሪ ገንዘብ ገቢ ማድረግና የውጭ ምንዛሬ መመንዘር የሚያስችል መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
ይህም ደንበኞች ገንዘብ ወደ ሂሳባቸው ገቢ ማድረግ እና የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚችሉበት አዲስ አሰራር መሆኑን ነው የኢቢሲ ዘገባ የሚያመለክተው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዲሱ ኤቲኤም / ATM /ማሽን በአሁኑ ሰዓት በሙከራ ደረጃ በባንኩ የፊንፍኔ ቅርንጫፍ ላይ ነው አገልግሎት መስጠት የጀመረው። ማሽኑ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ለይቶ ማስወገድ የሚችል መሆኑንም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋቢ አድርጎ ዘገባው አትቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ባንኩ ካሉት ከ22 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ 30 በመቶ የሚሆኑት የዲጅታል የክፍያ አማራጮችን የሚጠቀሙ መሆኑም ከባንክ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ከ 100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ የህብረተሰቡ ባንክ በሰፊው የመጠቀም ባህል ከቅርብ አመታት ወዲህ እየዳበረ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ በዲጂታል የገንዘብ ክፍያ እና ሌሎች ዘመናዊ የባንክ አሰራሮችን የሚጠቀመው የሀገሪቱ ህዝብ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡