ም/ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን ስለ አማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ምን አሉ?
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መምጣቱን አስታውቀዋል
አቶ ደመቀ የሁሉም ዋስትና ህግና ስርዓትን በተሟላ ሁኔታ ማስከበር ነው ብለዋል
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል አሉ ም/ጠ/ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን።
ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ይኖራሉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊና የውይይት አግባብ ነው ብለዋል በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።
ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ፣ ያለንን የሚያሳጣ እና በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ ሲሉም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ “የሀገር ሽማግሌ የጠፋ፣ መካሪ የሃይማኖት አባት የታጣ ይመስል ሁላችንንም የሚያባላና የሚበላ አካሄድ ይስተዋላል”ም ነው ያሉት አቶ ደመቀ።
ይህም “ከውጭና ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል” ሲሉም አክለዋል፡፡
የሁሉም ዋስትና የሆነውን ህግና ሥርዓት በተሟላ መልኩ ማክበርና ማስከበር እንደሚገባም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮነን ያሳሰቡት።
የፌደራል እና የክልሉ መንግስታት ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" በማካሄድ ላይ መሆናቸውን መግለጻው ይታወሳል።
የመከላከያ ሰራዊት በተሰማራባቸው በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተው ሰዎች መገደላቸውን እና በክልሉ ያለው ሁኔታ አሁንም የተረጋጋ አለመሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስቱር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ባሳለፍነው ማክሰኞ በሰጡት መግለጫም፤ ከሰሞኑ በአማራ ክልል ጎንደር ሰራዊቱ ላይ ሁለት ጊዜ ጥቃት እንደተሰነዘረበትም ገልጸዋል።
ሐምሌ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማካሄድ ጉዳዩ በይቅርታ መዘጋቱን በመግለጫቸው ጠቁመዋል።