በአማራ ክልል ምን እየተካሄደ ነው?
የፌደራል እና የክልሉ መንግስታት ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል
በክልል "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" ተጀመረ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የጸጥታ ሁኔታው ስለመባባሱ ነዋሪዎች ተናግረዋል
የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀቶች እንዲፈርሱ መወሰኑን ተከትሎ "የአማራ ልዩ ኃይል አይፈርስም" የሚሉ በርካታ ተቃውሞዎች መካሄዳቸው ይታወሳል።
- ልዩ ኃይል እንዲፈርስ መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል ተቃውሞ ተቀሰቀሰ
- በአማራ ክልል መከላከያ ሰራዊትና ታጣቂዎች በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
ተቃውሞውን ተከተትሎ በሚያዝያ 2015 ዓ.ም የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥታት በክልሉ "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" መጀመራቸውን ይፋ አድርገው ነበር።
ውሳኔውን በማይቀበሉ አካላት ላይ የህግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ ገልጾ የነበረው መንግስት መከላከያ ሰራዊትን በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች አሰማርቷል።
የመከላከያ ሰራዊት በተሰማራባቸው በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተው ሰዎች መገደላቸውን እና በክልሉ ያለው ሁኔታ አሁንም የተረጋጋ አለመሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የደብረወርቅ ነዋሪ እንዳሉን በምስራቅ ጎጃም ስር ባለችው እናርጅ እናውጋ ወረዳ ስር ባሉ ቀበሌዎች ከሁለት ሳምንት በፊት ጦርነት እንደነበር ነግረውናል።
በፖሊስ እና ፋኖ መሪዎች መካከል ተካሄደ ባሉት ጦርነት የ12 ሰዎች ህይወት ማለፉን የነገሩን እኝህ አስተያየት ሰጪ ከሟቾች ውስጥ አራቱ ንጹሀን አርሶ አደሮች እንደሆኑም ነግረውናል።
ደብረወርቅ ከተማ አሁን ላይ አንጻራዊ መረጋጋት ቢታይባትም የመንግስት ተቋማት አመራሮች ግን አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ከአንድ ሳምንት በፊት ከመርጦ ለማርያም ወደ ደብረማርቆ ከተማ መምጣቷን ጠቅሳ ፍጹም ሰላማዊ የነበረው ጎጃም አሁን ላይ የጦርነት ቀጠና መሆኑን አክላለች።
በተለይም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ወረዳዎች ለሕግ ማስከበር ዘመቻ ሲገባ ህዝቡ ከፍተኛ ፍርሀት እና መጠራጠር ውስጥ መግባቱንም ይህቺ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች ነዋሪ ነግራናለች።
"ፋኖ ማለት የአርሶ አደሮች ልጅ ነው" የምትለው ይህች ነዋሪ ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ መኖሪያ መንደሮች ሲገባ ልጆቼን ሊገድልብኝ ነው በሚል አርሶ አደሮች ልጆቻቸውን ለመከላከል ሲሞክሩ እየተገደሉ እና እየቆሰሉ መሆኑንም ገልጻለች።
ወቅቱ የአዝመራ ወቅት፣ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ የሚፈጸምበት ቢሆንም በአብዛኞቹ የጎጃም ወረዳዎች ጦርነት እየተካሄደ መሆኑንም ነዋሪዋ ነግራናለች።
አርሶ አደሮቹ ልጆቻችን በኦነግ ሸኔ እየታገቱ በሚልዮን ገንዘብ እየተጠየቅን እና እነሱን ለማስለቀቅ በየ ቤተ ዕምነቱ እየለመነ ባለበት ወቅት መንግሥት በአርሶ አደሩ ላይ ዘመቻ መክፈቱ እንዳሳዘናትም አክላለች።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በሰሜን ሸዋ ዞን ስር ባለችው ሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ ሲሆን አካባቢው በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ መሆኑን ነግሮናል።
ሸዋ ሮቢት እና በዙሪያው ያለው የቀወት ወረዳ ስር ያሉ ቀበሌዎች በተለይም የልዩ ሀይል መልሶ የማደራጀት እቅድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መልኩን ቀይሯል ብለውናል።
አካባቢው ባለፉት አራት ዓመታት አለመረጋጋት ቢኖረውም ካሳለፍነው ሚያዝያ ወር አንስቶ ግን ግጭቱ መልኩን መቀየሩን ሰምተናል።
መከላከያ ሰራዊት ለሕግ ማስከበር በሚል ወደ አካባቢው ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ነዋሪዎች በጸጥታ ሀይሎች እና በታጠቁ ሀይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን እኝህ ነዋሪ ነግረውናል።
በተለይም የፖሊስ አባላት፣ ፖሊስ ጣቢያዎች እና የጸጥታ አመራሮች ጥቃት እየተፈጸመባቸው ነው ያሉን እኝህ ነዋሪ ከጸጥታ ተቋማት እና አባላት ውጪ ያሉ ንጹሀንም እየሞቱ መሆኑንም አክለዋል።
እስካሁንም የፋኖ አባላት ናችሁ በሚል እና በተባራሪ ጥይት ተመተው ህይወታቸው ያለፉ ዜጎች ቁጥር ከ10 በላይ መድረሱን ይሄው ነዋሪ ጠቅሰዋል።
ሌላኛው በደቡብ ወሎ የደላንታ ወረዳ ወገል ጤና ከተማ ነዋሪ እና አስተያየት ሰጪ በበኩሉ ካለፉት 20 ቀናት ጀምሮ በደላንታ፣ ጉባ ላፍቶ፣ አምባሰል እና አማራ ሳይንት ወረዳዎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከፋኖ አባላት ጋር ጦርነት ውስጥ መሆኑን ነግሮናል።
አካባቢው ሰላማዊ ነበር የሚለን ይህ አስተያየት ሰጪ ካባለፉት 20 ቀናት አንስቶ ግን ህዝብ አለሙረጋጋት እና ፍርሀት ውስጥ መግባቱን አክሏል።
ወንጀል የሰሩ ሰዎች ቢኖሩ እንኳን በየወረዳው ካሉ መደበኛ ፖሊስ እና ሚሊሻ አቅም በላይ አልነበሩም ያለን ይህ ነዋሪ አሁን ላይ ሰዎች በሰላም መግባትና መውጣት እንዳልቻሉም ገልጿል።
ወገል ጤና ከተማ የትራንስፖርት እና ሌሎች የህዝብ አገልግሎቶች የሰዓት ገደብ መጣሉን፣ በተለይ ምሽት ላይ ከሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ እንደማይቻል፣ ሆቴሎች እና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ መሆናቸውንም ይህ ነዋሪ ነግሮናል።
ምሽት ላይ ሲንቀሳቀስ የተገኙ ሰዎችም ፋኖ ናችሁ በሚል እንደሚታሰሩ እና እንደሚደበደቡ የነገረን ነዋሪው ህግ የማስከበር ዘመቻው ህዝብን ሳያወያዩ መጀመሩ የመንግስት ትልቁ ስህተት መሆኑን አክሏል።
"የሀገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን እኛ መፍታት እንችላለን ፣ መከላከያ ሰራዊትም የፋኖ አባላትም የእኛው ልጆች ናቸው፣ የትኛውም ወገን አላስፈላጊ መስዋዕትነት እንዲከፍል አንፈልግም" ብለው ለአመራሮች ቢናገሩም የሚሰማቸው አልተገኘም ሲልም ይሄው ነዋሪ ነግሮናል።
የህዝብ ፍላጎት መንግሥት ለኑሮ ውድነት እና ለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ትኩረት እንዲሰጥ ቢሆንም መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ ህዝብ ለማወያየት እንኳን ፈቃደኛ አለመሆኑን ነዋሪው ጠቅሷል።
የአካባቢው ህዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካሳለፈው ጦርነት እና ዝርፊያ ለማገገም እየጣረ ባለበት ወቅት በህግ ማስከበር ስም ዳግም ወዳልተፈለገ ረብሻ እንዲገባ እያተደረገ ነው ሲሉም ይህ አስተያየት ሰጪ ነግሮናል።
አል ዐይን አማርኛ የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ እየተካሄዱ ስላሉ ጉዳዮች እና ከአስተያየት ሰጪዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽን ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም።
በተለይም የክልሉ ኮሙንኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ጥያቄ እንድንልክላቸው በጠየቁን መሰረት ጥያቄዎቹን ብንልክላቸውም ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን( ኢሰመኮ) ከወራት በፊት ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ሽዋ፣ በሰሜን ወሎ እኔ ሰሜን ጎንደር ዞኖች በመከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ታጣቂዎች ግጭት ተከስቶ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ ነበር። ኢሰመኮ ችግሩ በውይይት እንዲፈታም አሳስቦ ነበር።