ጎግል አፋን ኦሮሞና ትግርኛን ጨምሮ 10 በአፍሪካ የሚነገሩ ቋንቋዎችን በትርጉም አገልግሎቱ አካተተ
ጎግል በአጠቃላይ 24 አዳዲስ ቋንቋዎች በጎግል የትርጉም አገልግሎቱ ዝርዝሩ ውስጥ አካቷል
ጎግል በትርጉም አገልግሎቱ ያካተታቸው አዳዲስ ቋንቋዎች ከ300 ሚሊየን በላይ ተናጋሪ አላቸው
ጎግል አፋን ኦሮሞ እና ትግርኛን ጨምሮ 10 በአፍሪካ የሚነገሩ ቋንቋዎችን በትርጉም አገልግሎቱ (Google Translate) ዝርዝር ውስጥ ማካተቱን አስታውቋል።
ጎግል በአጠቃላይ በትርጉም አገልግሎቱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ 24 ቋንቋዎችን ማካተቱን ያስታወቀ ሲሆን፤ አገልግሎቱ ያካተታቸው አዳዲስ ቋንቋዎች ከ300 ሚሊየን በላይ ተናጋሪ ያላቸው ናቸው።
በትርጉም አገልግሎቱ የተካተቱ በአፍሪካ የሚነገሩ ቋንቋዎችም በኢትዮጵያ በስፋት የሚነገረው ኦሮምኛ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ የሚነገረው ትግርኛ፣ በማሊ የሚነገረው ባምባራ፣ በጋና እና በቶጎ ተናጋሪዎች ያሉት ኢዊ፣ በሴራሊዮን ተናጋሪዎች ያሉት ክሪዎ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንኮን ጨምሮ በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ተናጋሪወች ያሉት ሊንጋላ እንዲሁም በኡጋንዳ እና በሩዋንዳ ተናጋዎች ያሉት ሉጋንዳ ናቸው።
እንዲሁም ስፕሬዲ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቲዊ ከጋና እንዲሁም ትሶንጋ ከደቡብ አፍሪካ በጎግል ትርጉም (Google Translate) ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ የአፍሪካ ቋንቋዎች ናቸው።
ከአዲሶቹ ቋንቋዎች መካከል በሰሜን ህንድ፣ ኔፓል እና ፊጂ እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ ተናጋሪዎች ያሉት ቦጅፑሪ እንዲሁም በማልዴቪስ 300 ሺህ ህዝብ ተናጋሪ ያለው ድሂቨሪ ይገኙበታል።
ጎግል ከዚህ ቀደም አማርኛ፣ ሶማሊኛ እና ሀውሳን ጨምሮ በርካታ በአፈሪካ ውስጥ ተናጋሪ ያላቸው ቋንቋዎችን በጎግል ትርጉም ውስጥ በማካተት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ይታወሳል።
አሁን የተካተቱትን ቋንቋዎች ጨምሮ በጉግል ተርጓሚ የተካተቱ አጠቃላይ ቋንቋዎች ብዛት ወደ 133 ደርሷል።