አምነስቲ በአማራ ክልል የሚደረገው የጅምላ እስር እንዲቆም አለም አቀፍ ጫና እንዲደረግ ጠየቀ
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ያለ ክስ እና ፍርድ ቤት ሂደት ለወራት በእስር ላይ እንደሚገኙ ጠቁሟል
የኢትዮጵያ መንግስት የልማት አጋሮች መንግስት እስረኞችን እንዲፈታ አልያም በተገቢው መንገድ ክስ እንዲመሰርትባቸው ጫና እንዲያደርጉ አምነስቲ ጠይቋል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ አማራ ክልል እየተፈጸመ ነው ያለውን የጅምላ እስራት ለማስቆም አስቸኳይ አለም አቀፍ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቀረበ።
ድርጅቱ የሀገሪቱ መንግስት በክልሉ ሰፊ የእስር ዘመቻ ከጀመረበት መስከረም 2024 ጀምሮ አራት ወራት መቆጠራቸውን አመላክቷል፡፡
አምነስቲ ባወጣው መግለጫ እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 28 ቀን 2024 የኢትዮጵያ ፌዴራል እና የአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ግለሰቦችን ወደ አራት የጅምላ እስር ቤቶች በማጓጓዝ በክልሉ ውስጥ ማሰራቸውን ገልጿል።
እስር ከተፈጸመባቸው መካከል ዳኞች፣ አቃቤ ህጎች፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራንን ጨምሮ የፍትህ አካላት ይገኙበታል ነው የተባለው።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ማነስ ተችተዋል፡፡
ዳይሬክተሩ "በአማራ ክልል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዘፈቀደ ሲታሰሩ አለም አቀፍ ማህበረሰብ ዝምታን መምረጡ አሳፋሪ ነው፤ የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች ከአፍሪካ እና ከአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት አካላት ጋር በመሆን በግፍ የታሰሩ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሊጠይቁ ይገባል" ብለዋል፡፡
ቻጉታህ አክለውም “በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ያለምንም ክስ እና ፍርድ ቤት ለወራት አስሮ ማቆየት አይን ያወጣ የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው፤ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በዘፈቀደ የታሰሩትን ግለሰቦች በሙሉ በአስቸኳይ መፍታት ወይም አለም አቀፍ እውቅና ባላቸው ወንጀሎች መክሰስ አለባቸው” ብለዋል።
በቅርብ ወራት ውስጥ አራት የፍትህ አካላት በጥቅምት 2024 ተፈተዋል እንዲሁም ሶስት ዳኞች፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች እና ስር የሰደደ የጤና ችግር ያለባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእስር ቢለቀቁም አሁንም በሺዎች የሚቆየሩ ሰዎች ያለ ክስ እና ፍርድ በእስር ላይ እንደሚገኙ መግለጫው አመላክቷል፡፡
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ቀውስ ለመፍታት የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ጫና እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ ንጹሃን የጅምላ እስር እና ግድያ እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ተደጋጋሚ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመስከረም ወር አጋማሽ እስከ ታህሳስ ወር 2017 እንደሚሸፍን በገለጸውና ባለፈው ሳምንት ባወጣው ሪፖርቱ በአማራ ክልል 6 ሺ ሰዎች ለዘፈቀደ እስር ተዳርገዋል ብሏል።
ኢሰመኮ እንደገለጸው ዳንግላ፣ ጭልጋ፣ ኮምቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ዜጎች ከህግ ውጭ በጅምላ ታሰረው የሚገኙባቸው ቦታዎች ናቸው።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ በክልሉ 120 የሚሆኑ ንጹሃን መገደላቸውን ይፋ አድርጓል።
ሪፖርቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ እንደማይሸፍን የገለጸው ኢሰመኮ ግድያዎቹ በአብዛኛዎቹ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መፈጸማቸውን ጠቅሷል።