አምነስቲ በአማራ ክልል ከወር በላይ በጅምላ የታሰሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠየቀ
በክልሉ አራት ጊዜያዊ ካምፖች የታሰሩበትን ምክንያት በማያውቁ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ተጨናንቀዋል ብሏል ተቋሙ ባወጣው መግለጫ
ጊዜያዊ የማቆያ ጣቢያዎቹ በዳንግላ፣ ጭልጋ፣ ኮምቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት እንደሚገኙም አመላክቷል
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት ከአንድ ወር በላይ ለእስር የተዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።
ተቋሙ ከፈረንጆቹ መስከረም 28 2024 ጀምሮ አደረግኩት ባለው ማጣራት በክልሉ በአራት ጊዜያዊ የማቆያ ስፍራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ገልጿል።
“ኢትዮጵያ ብሄራዊ፣ ክልላዊ እና አለማቀፋዊ ሰብአዊ ግዴታዎቿን የመጣስ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ገብታለች፤ ባለፉት አምስት አመታት ከህግ አግባብ ውጪ የሆኑ የጅምላ እስሮች ሰላማዊ ጥያቄን ለማፈን እንደ ፖለቲካዊ መሳሪያ ጥቅም ላይ ሲውሉ ቆይተዋል፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የዚህ ከለላ ሲሆን ታይቷል” ብለዋል በተቋሙ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተሩ ቲገር ቻጉታህ።
“በአማራ ክልል እየታየ ያለው ህግን ያልተከተለ የጅምላ እስርም የተለመደ ታክቲክ ሆኗል” ነው ያሉት ዳይሬክተሩ።
አምነስቲ ከጊዜያዊ የማቆያ ጣቢያዎቹ የወጡ ሁለት ሰዎችን፣ አምስት የታሳሪ ቤተሰቦችን እና ዘጠኝ ከጅምላ እስሩ ጋር በተያያዘ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ማነጋገሩን ገልጿል።
በዚህም በዳንግላ፣ ሰራባ (ጪልጋ)፣ ኮሪሳ (ኮምቦልቻ) እና ሸዋ ሮቢት በተዘጋጁ ጊዜያዊ ጣቢያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ነው የጠቆመው።
ከዳንግላ ጊዜያዊ ማቆያ የተለቀቀ አንድ ግለሰብም በዳንግላው ካምፕ በግምት ከ1 ሺህ 600 በላይ ሰዎች መታሰራቸውንና እርሱ ሲለቀቅ ተጨማሪ ሰዎች መታሰራቸውን መናገሩን አምነስቲ በድረገጹ አስነብቧል።
በካምፑ ውስጥ የታሰሩት ሰዎች መብዛት መጨናነቅ በመፍጠሩም ተጨማሪ ቆርቆሮ በቆርቆሮ ክፍሎች እየተገነቡ መሆኑን ከእስር የተለቀቀው ግለሰብ መግለጹን ነው ያብራራው። አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በሳተላይት ምስሎች ተጨማሪ ክፍሎች መገንባታቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል።
“ዳኞችና መምህራን ኢላማ ተደርገዋል”
በአማራ ክልል ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል፣ ዳኞች፣ አቃቤ ህጎችና መምህራን ይገኙበታል። በተለይ የመንግስት ባለስልጣናት በፖለቲካዊ ክሶች ላይ እጃቸውን እንዳያስገቡ የተቃወሙ ዳኞች የእስሩ ሰለባ መሆናቸውን ነው የአምነስቲ ሪፖርት የጠቀሰው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ዳኛ ለተቋሙ ተናገሩ እንደተባለው ዘጠኝ ዳኛዎች እና የፍትህ ተቋማት ባልደረቦች እስካሁን በቁጥጥር ስር ናቸው፤ አራት ዳኞች ከሁለት ሳምንት በፊት ተለቀዋል።
“አብዛኞቹ የታሰሩት ዳኞች ከፍርድቤት ተይዘው ነው ወደ ጊዜያዊ ካምፖቹ የተወሰዱት፤ ጥቂቶቹ ከቤታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል” የሚሉት አስተያየታቸውን ያጋሩ ግለሰብ፥ አብዛኞቹ ለምን እንደታሰሩ እስካሁን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቃቤ ህግም በክልሉ 13 አቃቢያነ ህግ መታሰራቸውንና ከሁለት ሳምንት እስከ አንድ ወር ድረስ ፍርድቤት አለመቅረባቸውን አብራርተዋል ብሏል የአምነስቲ ሪፖርት።
“ለ30 አመት ገደማ በፍትህ ስርአቱ ውስጥ አገልግያለሁ፤ እንዳሁኑ አይነት ህገወጥነት ግን አይቼ አላውቅም” የሚሉ ምንጩንም ሃሳብ አካቷል።
“ከዚህ ቀደም በሚደረጉ የጅምላ እስሮች ሲደረጉ ተጠርጣሪዎች በአንድ ወይ በሁለት ቀን ፍርድቤት ይቀርቡ ነበር፤ የታሰሩት ሰዎችም ምንም እንኳን ምክንያቱ የተቀነባበረ እንደሚሆን ቢያውቁትም ለምን እና ማን እንዳሳሰራቸው ይጠይቁ ነበር፤ አሁን ግን ማን እንዲታሰሩ እንዳዘዘና መቼ እንደሚለቀቁም አያውቁም” ሲሉም አብራርተዋል።
አንድ ከእስር የተለቀቀ ግለሰብም “ጠዋት ሌሎች ሰዎችን በቁጥጥር ሲያውል የነበረ ፖሊስ ከስአት በኋላ ተይዞ ታስሯል፤ ከፍተኛ አዛዦችም እኔ በታሰርኩበት ክፍል ተመልክቻለሁ” ማለቱ ተጠቁሟል።
መምህራንም የጅምላ እስሩ ሰለባ መሆናቸውን የሚጠቅሰው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፥ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ብቻ 11 መምህራን መታሰራቸውን ከታማኝ ምንጮች አረጋግጫለሁ ብሏል። በኮሪሳ (ኮምቦልቻ) ጊዜያዊ የማቆያ ጣቢያ ታስረው የነበሩት መምህራን ከአንድ ወር እስር በኋላ በዚህ ሳምንት ፍርድቤት መቅረባቸውንም በመጥቀስ።
የአምነስቲ የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተሩ ቲገር ቻጉታህ በፍትህ እና ትምህርት ተቋማት ሰራተኞች እንዲሁም በጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ ያነጣጠረው የጅምላ እስር “እጅግ አሳሳቢ” ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ብሎም የአለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት በአማራ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የጅምላ እስር እንዲያወግዙትም ነው ያሳሰቡት።
አምነስቲ በአራት ከተሞች በሚገኙ ጊዜያዊ ካምፖች የታሰሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “የተሃድሶ ስልጠና” ወስደው ካጠናቀቁ በኋላ ይለቀቃሉ መባሉን ከታሳሪ ቤተሰቦች መስማቱን ገልጿል።