በአማራ ክልል በሶስት ወራት ውስጥ 120 ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ
በክልሉ የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች በዘፈቀደ እስር ላይ እንደሆኑም ተገልጿል
በኦሮሚያ ክልልም ከ80 በላይ ንጹሃን እንደተገደሉ ኢሰመኮ አስታውቋል
በአማራ ክልል በሶስት ወራት ውስጥ 120 ንጹሀን ዜጎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ ክልሎች ያደረጋቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚሽኑ እንደለጸው ሪፖርቱ ከመስከረም ወር አጋማሽ 2017 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 2017 ዓ.ም አጋማሽ ባለው ጊዜ ውስጥ ያለውን ጊዜ የሚመለከት ነው ብሏል፡፡
ሪፖርቱ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በሙሉ የሚሸፍን አይደለም ያለው ኮሚሽኑ በእነዚህ አካባቢዎች በነጻነት ተንቀሳቅሶ የተሟላ ክትትልና ምርመራ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ፣ ውጤታማ ክትትልና ምርመራ የተከናወነባቸውን ጉዳዮች ብቻ በማሳያነት እንዳቀረበም ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ እንደጠቀሰው በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ከደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ ሆነው ከቀጠሉ ጉዳዮች መካከልም ከፍርድ ውጭ ግድያ መፈጸም፣ በግጭት ዐውድና አካባቢ የሚደርስ የሲቪል ሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና ዘረፋ ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እስራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ፣ በመዘዋወር መብትና በመጓጓዣ መንገዶች ላይ የሚፈጸም ሕገ-ወጥ ገደብ፣ የሀገር ውስጥ መፈናቀል እና የዳኝነት ነጻነት መሸርሸሮች እንዳሉም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡
በአማራ ክልል በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከ120 በላይ ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ የገለጸው ኢሰመኮ ግድያው በአብዛኛው በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የተፈጸመ ሲሆን የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ እንደፈጸሙ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ፋኖ ናችሁ እና ለፋኖ ትረዳላችሁ በማለት ንጹሃንን ሲገድሉ የፋኖ ታጣቂዎች ደግሞ የመንግስት አገልጋዮች ናችሁ በሚል ግድያውን ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይኖሩ የነበሩ 84 ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ንጹሃኑ የተገደሉት በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና በተለምዶ ኦነግ ሸኔ ተብለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን አባላት ሲሆን የመንግስት የጸጽታ ሀይሎች ለኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ትረዳላችሁ እያሉ ግድያውን ፈጽመዋል ተብሏል፡፡
የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ደግሞ መንግስትን ትረዳላችሁ በሚል ንጹሃን ዜጎችን እንደሚገድሉ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች የዘፈቀደ እስር እየፈጸሙ እንደሆነ እና በአማራ ክልል ብቻ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች ዳንግላ፣ ጭልጋ፣ ኮንቦልቻ እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ከህግ ውጪ በእስር ላይ ናቸው ተብሏል፡፡