በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎችን ያለፈቃዳቸው መያዝና ወደ ማቆያ ማዕከላት ማስገባት ሊቆም ይገባል-ኢሰመኮ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ወደ ማቆያ የሚገቡ ሰዎች በማዕከሉ ከመቆየት እና የእርሻ ሥራ ከመሥራት እንዲመርጡ እየተደረጉ ነው ብሏል
ድርጊቱ የሰዎቹን የነጻነት መብት ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ በመሆኑ እንዲቆም ጠይቋል
በጎዳና ላይ ያሉ ሰዎችን ያለፈቃዳቸው መያዝና ወደ ማቆያ ማዕከላት ማስገባት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ስለሚያስከትል ሊቆም ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ጉባኤዎች እንዲሁም ከሌሎች ተመሳሳይ ኹነቶች ጋር በተያያዘ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎችን በኃይል በማንሳት በአንድ ስፍራ እንዲቆዩ የማድረግ ስራ በተደጋጋሚ እንደሚከናወን መግለጫው አመላክቷል፡፡
ኢሰመኮ በታኅሣሥ ወር 2017 ዓ.ም ባደረጋቸው ክትትሎች በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ “ቃሊቲ አካባቢ” ተብሎ በሚጠራው የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አካባቢ ሰፊ መጋዘን ውስጥ ከጎዳና ላይ የተነሱ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ወደ ማቆያው ከገቡት ሰዎች መካከል በማዕከሉ ከመቆየት እና የእርሻ ሥራ ከመሥራት እንዲመርጡ በማድረግ፤ የእርሻ ሥራ ለመሥራት የመረጡ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ወደሚገኙ እርሻ ጣቢያዎች ተወስደው እንዲሠሩ እንደሚደረግ ነው የተገለጸው፡፡
በዚህም ድርጊቱ የነጻነት መብታቸውን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
ችግሩ የፖሊሲ መፍትሔ የሚያሻው ነው ያለው የኢሰመኮ ሪፖርት ወደመጡባቸው አካባቢዎች የመመለስ እና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ሰብአዊ መብቶቻቸውን ባከበረ መልኩ ማከናወን ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባለፈም በጊዜያዊ ማቆያ ማዕከሉ ከንጽሕና እና ከጤና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ በሰዎች ሕይወትና ጤና ላይ አደጋ የሚጥሉ ሁኔታዎች እንዳይፈጠር፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር ውይይቶችን በማድረግ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እገኛለሁ ብሏል፡፡
የኢሰመኮ ተጠባባቂ ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ወደማቆያ በፈቃደኝነት ለሚገቡ ሰዎች የሚዘጋጁ የተሐድሶ ማዕከላት መሠረተ ልማት የተሟላላቸው፣ ንጽሕናቸው የተጠበቀ፣ ለደኅንነት እና ለጤና ሥጋት የማይፈጥሩ ተደርገው የተዘጋጁ መሆናቸው ሊረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።