አምነስቲ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ቱርክ ኤርትራውያን ስደተኞችን በሀይል ከሀገር እያስወጡ ነው ሲል ከሰሰ
ባለፉት 3 ወራት ብቻ 600 ኤርትራውን ከኢትዮጵያ ተገደው ወደ ኤርትራ መላካቸውን ማረጋገጡንም ገልጿል

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ጉዳዩን እንዲያወግዘው ጠይቋል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ኤርትራውን ስደተኞችን በሀይል ከሀገር የምታስወጣበትን ድርጊት እንዲያወግዝ ጠየቀ፡፡
ድርጅቱ በ58ኛው የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በንባብ ባቀረበው መግለጫ ባለፉት 3 ወራት ብቻ 600 ኤርትራውን ስደተኞች በአስገዳጅ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ መላካቸውን አመላክቷል፡፡
ባለፈው አንድ አመት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የኤርትራ ስደተኞችን በዘፈቀደ ማሰር እና ማፈናቀልን በተመለከተ ጥቆማዎችን ሲከታተል እና ሪፖርቶችን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጿል፡፡
የኤርትራ ስደተኞች የሰብአዊ መብት አያያዝ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሱዳንም ከፍተኛ ችግር እያጋጠመው እንደሚገኝ አምነስቲ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
በሱዳን በቀጠለው ግጭት ምክንያት በተለይ የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ ተቆጣጥሯቸው በሚገኙ ስፍራዎች ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ ስደተኞች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እያስተናገዱ ይገኛሉ ነው የተባለው፡፡
በተጨማሪም በነሀሴ 2024 ቱርክ ወደ 180 የሚጠጉ ኤርትራውያንን በግዳጅ ወደ ኤርትራ መመለሷን እንዲሁም ጥገኝነት እና ከለላ የማግኘት ህጋዊ መብታቸውን ጥሳለች በሚል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ወቅሷል፡፡
አስርተ አመታትን ያስቆጠረው አስገዳጅ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት፣ ከባባድ የጉልበት ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ፖለቲካዊ ሁኔታዎች አሁንም በርካታ ኤርትራውን ሀገራቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነው መቀጠላቸው ተነስቷል፡፡
አምነስቲ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለውን ውጥረት ተከትሎ በየካቲት ወር አስመራ ተጨማሪ ወታደሮችን ለመመልመል በእንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ከታማኝ ምንጮች ማረጋገጡን አስታውቆ፤ ሁኔታው ከኢትዮጵያ በግዳጅ ወደ ኤርትራ የሚላኩ ስደተኞችን ለአደጋ ተጋላጭነት እንደሚጨምረው አመላክቷል፡፡
በዚህም ሁሉም የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባላት የኤርትራውን ስደተኞችን አስገዳጅ ማባረር፣ እስር እና የመብት ጥሰትን እንዲያወግዙ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል በኤርትራ ዜጎች መብት ጥሰት እና ከአለም አቀፍ ህግ አፈጻጸም አኳያ በምክር ቤቱ የተቋቋመው ልዩ አጣሪ ኮሚቴ ከተመሰረተ ዘጠኝ አመት ቢያስቆጥርም በሀገሪቱ ያሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ አሁንም አለመሻሻሉ እንደሚያሳስበው ነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያስታወቀው።
በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ለቀረበው ወቀሳ የኢትዮጵያ መንግስት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም፡፡