ኤርትራ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ለቀረበባት ክስ ምን ምላሽ ሰጠች?
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል "የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል" ብለዋል

ዶክተር ሙላቱ "የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ እየተዘጋጀ ነው" የሚል ጽሁፍ አልጀዚራ ላይ ማስፈራቸው ይታወሳል
ኤርትራ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለቀረበባት ክስ ምላሽ ሰጠች።
የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የተነሱትን ነጥቦች አጣጥለዋል።
ዶክተር ሙላቱ ከሁለት ቀናት በፊት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ግጭት እንዳይከፈት ለማስቆም ጊዜው አሁን ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
"ጦርነት የኤርትራ መንግስት ዋናኛ ቢዝነስ ነው" የሚሉት ዶክተር ሙላቱ፥ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ባለፉት 30 ዓመታት በተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ ግጭቶች መሳተፋቸውን በጽሁፋቸው አብራርተዋል።
የትግራዩን ጦርነት "እንደ እድል በመጠቀም"ም ወታደሮቻቸውን ወደ ክልሉ አስገብተው "ውድመት" ማስከተላቸውን በመጥቀስ፥ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ "መሰናክል" ፈጥሯል ሲሉም ያትታሉ።
ፕሬዝዳንቱ ተጽዕኗቸውን የሚያሰፉት በግጭት በመሆኑ ሰላም እንቅፋት ይሆንባቸዋል፤ በትግራያ ክልል ማቆሚያ የሌለው ግጭት እንዲኖር ይፈልጋሉ፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት ደስተኛ ካልሆኑ የህወሃት አመራሮች ጋር እየሰሩ ነው በማለትም ከሰዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ የሚከሰት ችግር ለቀጠናው ስለሚተርፍ አለማቀፉ ማህበረሰብ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ይደረግ ዘንድም ጠይቀዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ትናንት በዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለቀረቡት ክሶች ምላሽ ሰጥተዋል።
"ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ግጭት እየቀሰቀሰች ነው" በሚል በዶክተር ሙላቱ የቀረበው ክስ ሀሰተኛ እና በተለመደው "ጥንታዊ ፋሽን" የቀረበ ነው በሚል ውድቅ አድርገውታል።
ከቀረቡት ክሶች በተቃራኒው ቀጠናውን ለከበቡች ችግሮች "ማዕከሏ ኢትዮጵያ ናት" ያሉት ሚኒስትሩ፥ ጥሬ ሀቁን ያሳያሉ ያሏቸውን 10 ነጥቦችም በኤክስ ገጻቸው ላይ ዘርዝረው አቅርበዋል።
ዶክተር ሙላቱ "ታሪካዊ ሁነቶችን አዛብተው አቅርበዋል" በሚል የከሰሱት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፥ ሀገራቸው በትግራዩ ጦርነት የተሳተፈችው "ህወሃት በኤርትራ ላይ መጠነሰፊ ሊያደርስ ጥቃት ስለነበር እና የፌደራሉ መንግስት የድጋፍ ጥያቄ በማቅረቡ" መሆኑን አውስተዋል።
ኤርትራ ከህወሃት ጥቃት ላመለጡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መሸሸጊያ እንደነበረችና "በኢትዮጵያ የጨለማ ጊዜ ለነበራት የማይተካ ሚና በኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ተሰጥቷት እያለ (በዶክተር ሙላቱ) የቀረበባት ክስ አሳፋሪ ነው" ሲሉም ወቅሰዋል።
የትግራዩን ጦርነት ለማስቆም የተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት "የኢትዮጵያ መንግስት የውስጥ ጉዳይ" በመሆኑ "ኤርትራ ስምምነቱን የማደናቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት የላትም" ሲሉም ክሱን ውድቅ አድርገዋል።
ኤርትራ ወታደሮቿን በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው ሉዓላዊ ድንበሯ ውስጥ እንደገና ማሰማራቷን ጠቅሰው፥ የኤርትራና ኢትዮጵያ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔን "በቅን ልቦና ያልተቀበሉ ወይም ግጭት ለመፍጠር ዓላማ ያላቸው አካላት" የኤርትራ ወታደሮች እንደ ባድመ ባሉ የድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ የሚሉ "ሐሰተኛ ውንጀላዎችን" እያቀረቡ ነው ብለዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጽሁፍ ውድቅ ከማድረግ ባሻገር በኢትዮጵያ መንግስት ላይም ክስ አቅርበዋል።
ባለፉት ወራት የኢትዮጵያ መንግስት በኤርትራ ላይ "ምክንያት የለሽ እና የተጠናከረ የትንኮሳ ዘመቻ ከፍቷል" ያሉት የማነ ገብረመስቀል፥ የትንኮሳው አላማ ከተቻለ በህጋዊ ካስፈለገም በወታደራዊ መንገድ ወደቦችን እና የባህር በር የማግኘት አጀንዳን ለማሳካት ሊሆን እንደሚችልም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመውን የመግባቢያ ስምምነት "የተድበሰበሰና በቀጠናው ውጥረት መፍጠሩን ቀጥሏል" ያሉት ሚኒስትሩ፥ በአማራ ክልል የማያባራ ጦርነት መቀስቀሱም ቀጠናውን ለከበቡት ችግሮች መፍለቂያዋ ኢትዮጵያ መሆኗን ሌላኛው አመላካች ጉዳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለውስጣዊ ችግሮቿ "ኤርትራን እንደ ማምለጫ መንስኤ" መጥቀሷን ከቀጠለች መፍትሄ አታገኝም ሲሉም በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የቀረበውን ክስ ተከላክለዋል።