የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በኤርትራ ጉዳይ የሰጡት ሀሳብ የመንግስት አቋም አለመሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ
ኢትዮጵያ አሁንም የወደብ ፍላጎቷ ላይ የአቋም ለውጥ አላደረገችም ተብሏል

በማይናማር ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ አሁንም ጥረት እያደረገ መሆኑን ሚንስቴሩ አስታውቋል
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በኤርትራ ጉዳይ የሰጡት ሀሳብ የመንግስት አቋም አለመሆኑን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫው ላይ ከጋዜጠኞች ከቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከል የቀድሞው የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ሙላቱ (ዶ/ር) ኤርትራን አስመልክቶ ያጋሩት ጽሁፍ ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከሁለት ሳምንትት በፊት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ "የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነት ለመቀስቀስ እየተንቀሳቀሰ ነው፤ በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ግጭት እንዳይከፈት ለማስቆም ጊዜው አሁን ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ በቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የተነሱትን ነጥቦች አጣጥለዋል።
ስለ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጽሁፍ እና የኤርትራ መንግሥት ምላሽ የተጠየቁት አምባሳደር ነቢያት "የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስተያየት የግላቸው እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም አይደለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የትግራዩን ጦርነት "እንደ እድል በመጠቀም"ም ወታደሮቻቸውን ወደ ክልሉ አስገብተው "ውድመት" ማስከተላቸውን በመጥቀስ፥ ጦርነቱን ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግን ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ "መሰናክል" ፈጥሯል ሲሉም ያትታሉ።
ፕሬዝዳንቱ ተጽዕኗቸውን የሚያሰፉት በግጭት በመሆኑ ሰላም እንቅፋት ይሆንባቸዋል፤ በትግራይ ክልል ማቆሚያ የሌለው ግጭት እንዲኖር ይፈልጋሉ፤ በፕሪቶሪያው ስምምነት ደስተኛ ካልሆኑ የህወሃት አመራሮች ጋር እየሰሩ ነው በማለትም ከሰዋል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት አልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፋቸው በኢትዮጵያ የሚከሰት ችግር ለቀጠናው ስለሚተርፍ አለማቀፉ ማህበረሰብ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ይደረግ ዘንድም ጠይቀዋል።
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለቀረቡት ክሶች ምላሽ ሲሰጡ፥ "ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ግጭት እየቀሰቀሰች ነው" በሚል የቀረበው ክስ ሀሰተኛ እና በተለመደው "ጥንታዊ ፋሽን" የቀረበ ነው በሚል ውድቅ ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው።
በዛሬው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት አንዱ ነበር።
ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በፊት ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው የወደብ ስምምነት እንዴት ሆነ? የሚል ሲሆን ቃል አቀባዩ አምባሳደር ነቢያት በምላሻቸው ላይ ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት እና የትብብር ጉዳዮችን ለማሳደግ መስማማታቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ "ኢትዮጵያ የወደብ ፍላጎቷን በሰጥቶ መቀበል መርህ ለማግኘት የጀመረችው ጥረት አሁንም አልተወችውም" ብለዋል።
በህገወጥ ደላሎች ተታለው ወደ ታይላንድ እና ማይናማር የሄዱ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ቶኪዮ እና ኒው ዴልሂ ባሉ ኢምባሲዎች በኩል ጥረቱ እንደቀጠለ ነውም ተብሏል።