ከመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ታጋቾች 7ቱ መለቀቃቸው ተገለጸ
ከህወሓት ተልዕኮ ተቀብለው ይንቀሳቀሱ በነበሩ ሽፍቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ 16 ያህሉ መደምሰሳቸውን ተገልጿል
ታጋቾቹ በአካባቢው ከተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እውቅና ውጪ ሲንቀሳቀስ በነበረ አካል ታጅበው ወደ ማንቡክ ሲጓዙ ነበር ተብሏል
ከመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ታጋቾች 7ቱ መለቀቃቸው ተገለጸ
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ከታገቱ ሰዎች መካከል 7ቱ መለቀቃቸውን የዞኑ የኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌው በየነ በተለይ ለአል ዐይን አማርኛ ተናገሩ፡፡
ኮሎኔሉ ታጋቾቹ ከኮማንድ ፖስቱ እውቅና ውጪ በክልሉ ልዩ ሃይል ታጅበው በአይሱዚ ሲጓዙ መታገታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የታገቱት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እና በአሁኑ ሰዓት ታግተው የሚገኙ ሰዎች ስለመኖራቸው በውል የተረጋገጠ ነገር የለም እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፡፡
ታጋቾቹን በተመለከተ የተለያዩ የቁጥር መረጃዎች እንደሚሰጡም ነው የገለጹት፡፡ ቀሪ ታጋቾች ካሉ ለማስለቀቅ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ከአካባቢው ሌሎች ምንጮች ለማረጋገጥ እንደቻለው ከሆነ ከትናንት በስቲያ ጀምረው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ ጉብላክ ከተሰኘችው የገጠር ከተማ ተነስተው 35 ኪሎ ሜትሮችን ወደምትርቀው ወደ ዳንጉር ወረዳ ማዕከል ማንቡክ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ 8 የጤና ባለሙያዎች አጅቧቸው ሲጓዝ በነበረ የክልሉ ልዩ ኃይል ታግተዋል፡፡
እገታው ወደ ስፍራው አቅንተው ወደ ዞኑ ማዕከል ግልገል በለስ ከተማ ይመለሱ የነበሩ መካኒክ የጋራዥ ባለሙያዎችንም ያካተተ ነው፡፡
ከሰሞኑ ከነ ትጥቃቸው የክልሉን ልዩ ኃይል ከድተው የወጡ አባላት እንዳሉ ተሰምቷል፡፡ እገታው ምናልባትም በእነዚሁ አካላት ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችልም ነው ሰብሳቢ የተናገሩት፡፡
አጋቾቹ ከህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ሽፍቶች ናቸው ያለው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቀደም ሲል በማህበራዊ ገጹ ባወጣው መረጃ 16 ያህሉ መደምሰሳቸውን አስታውቋል፡፡
ቀሪዎቹን ለመደምሰስ የሚያስችል ዘመቻ በመካሄድ ላይ ይገኛልም ነው ያለው፡፡
የኮማንድ ፖስቱ ሰብሳቢ ኮሎኔል አያሌውም ይህንኑ መረጃ መውሰድ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡