በገዳሪፍ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሱዳን ድንበር ላይ ተያዘ
ጦር መሳሪያው በሱዳን ጦር የደፈጣ ኦፕሬሽን የተያዘ ነው ተብሏል
መሳሪያው በአህያ ጋሪ ተጭኖ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ነበር የተባለ ሲሆን መዳረሻው የትኛው የሃገሪቱ አካባቢ ስለመሆኑ የተገለጸ ነገር ግን የለም
በገዳሪፍ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ሱዳን ድንበር ላይ ተያዘ
በአህያ ጋሪ ተጭኖ በገዳሪፍ በኩል በህገ ወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ የነበረ 95 ሺ ጥይት መያዙን የሱዳን ጦር አስታወቀ፡፡
ጦሩ ጋሪዎቹን ለመያዝ ባደረገው የደፈጣ ቁጥጥር ነው የተለያዩ አደንዛዥ እጾችን ጨምሮ ጥይቶቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው፡፡
የጦሩ ደህንነት በደረሰው መረጃ መሰረት የቁጥጥር ኦፕሬሽኑን መፈጸሙንም ነው የሃገሪቱ የዜና አገልግሎት (ሱና) የዘገበው፡፡
በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው እና ቁራይሻ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባደረገው ደፈጣም ጥይቶቹን በፕላስቲክ ቁሳቁሶች ሸሽገው ሲያጓጉዙ የነበሩ ተጓዦችን ይዟል፡፡
ጦሩ ጥይቶቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው በሰሜናዊ ኢትዮጵያ በመንግስት ጦር እና በህወሓት ሃይሎች መካከል ውጊያ በተቀሰቀሰበት ወቅት ነው፡፡
ሆኖም የህገወጥ መሳሪያዎቹ መዳረሻ የት ሊሆን እንደሚችል በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡
ገዳሪፍ የተሰኘው የሱዳን ግዛት ከትግራይ እና የአማራ ክልሎች ጋር ይዋሰናል፡፡
የመከላከያ ሠራዊቱ ከሱዳን ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን ዳንሻን ጨምሮ ባከርን እና ከሽራሮ እስከ ሽሬ ያሉ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ትናንት አስቸኳይ ስብሰባውን ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ማዘዙም አይዘነጋም።