ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው ተሾሙ
በተያያዘ ዜና አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾመዋል
ያለፉትን 12 ገደማ ዓመታት ከጦሩ ተለይተው ያሳለፉት ጄነራሉ ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐቢይ መጠራታቸው ይታወሳል
ከሰሞኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠሩት ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሆነው ተሾሙ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መከላከያ ሰራዊቱን እንዲቀላቀሉ ከሰሞኑ ጥሪ ያደረጉላቸውን ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰን የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አድርገው ሾሙ፡፡
የጄነራል ማዕረጉን ባገኙበት ወቅት በእድሜ ትንሹ የጦር መሪ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ በተለያዩ የጦሩ የሃላፊነት እርከኖች ላይ በማገልገል እና በለውጡ ፈርሶ ወደ ደቡብ እዝነት እንዲቀየር የተደርገውን ማዕከላዊ እዝን በመምራት ይታወቃሉ፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በባድመ ግንባር በኩል ትልቅ ወታደራዊ ጀብድ እንደፈጸመ የሚነገርለትን ክፍለ ጦር መርተው ለድል አብቅተዋልም ይባላል፡፡
ሆኖም ሌ/ጀኔራል አበባው ከ2006 ዓ/ም ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከተጠሩበት ጊዜ ድረስ በጡረታ በሚል ከጦሩ ተገልለው ቆይተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሆነው ተሹመዋልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆኑ ሌሎች ተጨማሪ ሹመቶችንም ሰጥተዋል፡፡
በሹመቱ መሰረትም
- አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
- ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
- ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
- አቶ ተመስገን ጥሩነህ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር
- ኮሚሽነር ደመላሽ ገ/ሚካኤል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሆነው ተሾመዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሾመዋል::
አሁን ባለው ሃገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ለሌላ ሃገራዊ የስራ ኃላፊነት መፈለጋቸውን ተከትሎ የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄያቸውን መደበኛ ጉባዔውን በማካሄድ ላይ ላለው የአማራ ክልል ምክር ቤት ያቀረቡት ርዕሰ መሥተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ መልቀቂያውን ያስገቡት የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በመሾማቸው ነው፡፡
ከአሁን ቀደም በኢትዮጵያ መረብ ደህንነት ኤጀንሲና በሌሎችም የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉት አቶ ተመስገን በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ከመሾማቸው በፊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር በመሆን ሰርተዋል፡፡
ጥያቄያቸውን የተቀበለው የክልሉ ምክር ቤትም በአማራ ብልጽግና ፓርቲ የእጩ መስተዳድር ሹመት አጽድቋል፡፡
በመሆኑም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ሆነው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል፡፡