ዩኤኢ በየመን እና በሊቢያ ሰላም ለማውረድ የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ አስታወቀች
ሀገሪቱ ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ለሀገራት የምታደርገውን ድጋፍ እንደምትቀጥል አስታውቃለች
ቱርክ እና ኢራን ቀጣናውን ከማተራመስ እንዲቆጠቡም የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሳስበዋል
ቱርክ እና ኢራን ቀጣናውን ከማተራመስ እንዲቆጠቡም የዩኤኢ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሳሰቡ
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ / ር አንዋር ቢን ሙሐመድ ጋርጋሽ አገራቸው በየመን ያለውን የአረብ ጥምረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ዛሬ ባደረጉት ንግግር አረጋግጠዋል፡፡ በሀገሪቱ ሙሉ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በቀጣናው የተፈጠሩ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የተሻለ እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
በየመን ለተፈጠረው ቀውስ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ቁርጠኛ ነን ብለው የአረብ ጥምረትን መደገፋችንን በመቀጠል በሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ የተኩስ አቁም ለማድረግ እንጥራለን ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡
የሊቢያ ቀውስ
በሊቢያ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ያደነቁት ዶ/ር አንዋር ፣ በሀገሪቱ ያለውን ቀውስ ለመፍታት የተባበሩት መንግስታት እያደረገ ያለውን ጥረት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንደምትደገፍ ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ ይህን ያሉት በኤምሬትስ የፖሊሲ ማእከል በተዘጋጀው “ሰባተኛው የአቡ ዳቢ ስትራቴጂክ ፎረም 2020” ን ለማስጀመር ባደረጉት ንግግር ላይ ነው ፡፡
ቱርክ እና ኢራን ቀጣናውን ከማተራመስ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ የአንካራም ሆነ የቴህራን ተግባር ለቀጣናው በሙሉ አስከፊ መሆኑን ያነሱት ጋርጋሽ “ቱርክ እና ኢራን የሀገራትን ብሄራዊ ሉዓላዊነት እንዲያከብሩ እና በቀጣናው ሀገራት ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ” አሳስበዋል፡፡
“የተባበሩት መንግስታት በሊቢያ የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን ፤ የሀገሪቱን የተኩስ አቁም ስምምነትም በደስታ እንቀበላለን” ሲሉም ነው ዶ/ር አንዋር ጋርጋሽ የገለጹት፡፡
ኮሮና እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሰብአዊ ድጋፍ
በሌላ በኩል ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታው ካለፈው ታህሳስ መጨረሻ ጀምሮ በዓለም ላይ ተባብሶ የቀጠለውን የኮሮና ወረርሽኝ የተመለከቱ ሲሆን ሀገራቸው ቫይረሱን ለመቆጣጥር የሚደረገውን ጥረት እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡
ኢራንን ጨምሮ ለበርካታ ሀገራት ዩኤኢ የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጓንም የገለጹት ጋርጋሽ ሀገራቸው በቀጣይነትም የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተለያዩየህክምና ግብአቶችን እና ሌሎች ድጋፎችን ለሚያስፈልጋቸው ሀገራት መላክን ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር እየሰራች መሆኑን ነው የጠቀሱት፡፡ ቫይረሱን መከላከል የሚቻለው በጋራ ጥረት ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም አጠቃላይ የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር ከ 50.8 ሚሊዮን የበለጠ ሲሆን ከ 35.8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ሲያገግም ከ 1 ሚሊዮን 263 ሺህ በላይ የሚሆኑት ህይወታቸው አልፏል፡፡