"ዩናይትድ ከፕሪሚየር ሊጉ ላለመውረድ ትግል ላይ መሆኑ ግልጽ ነው" - አሞሪም
ቀያይ ሰይጣኖቹ ትናንት ምሽት በኒውካስትል መሸነፋቸውን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው ያላቸው የነጥብ ልዩነት ሰባት ሆኗል
ማንቸስተር ዩናይትድ ከፕሪሚየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የወረደው በ1973/74 የውድድር አመት ነበር
ማንቸስተር ዩናይትድ ከፕሪሚየር ሊጉ ሊወርድ እንደሚችል አሰልጣኙ ሩበን አሞሪም ተናገሩ።
አሰልጣኙ ትናንት ምሽት በኦልትራፎርድ በኒውካስትል 2 ለ 0 ከተሸነፉ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ክለባቸው ላለመውረድ ትግል ላይ መሆኑን አምነዋል።
ቀያይ ሰይጣኖቹ በሜዳቸው ሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሲሸነፉ ከ1979 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ሶስት የሊግ ጨዋታዎችን ሲሸነፉ ደግሞ ከ2015 በኋላ የትናንቱ የመጀመሪያ ነው።
በኒውካስትል መሸነፋቸውን ተከትሎ ከሶስተኛው ወራጅ ክለብ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት ዝቅ ብሏል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከፕሪሚየር ሊጉ ለመጨረሻ ጊዜ የወረደው በ1973/74 የውድድር አመት ነበር።
አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ከኒውካስትሉ ሽንፈት በኋላ ክለቡ ከ50 አመት በኋላ ከፕሪሚየር ሊጉ ሊወርድ ይችላል ወይ ተብለው ተጠይቀው "በጣም ግልጽ ይመስለኛል፤ ዩናይትድ በታሪኩ ከባድ ከሆኑ ጊዜያት ውስጥ አንዱን እያሳለፈ ነው፤ ይህን በግልጽ መናገር አለብን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"የዩናይትድ አሰልጣኝ ሆኖ በርካታ ጨዋታዎችን መሸነፍ በጣም ያሳፍራል" ያሉት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ፥ ለቡድኑ ውጤት ማጣት ተጠያቂ መሆናቸውን መናገራቸውንም ስካይ ኒውስ አስነብቧል።
ማንቸስተር ዩናይትድ የሊጉን አጋማሽ በ22 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፤ 18ኛ ደረጃን ከያዘው ኢፕስዊች ታውን ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ሰባት ብቻ ነው።
ቀያይ ሰይጣኖቹ በአዲሱ የፈረንጆቹ አመት 2025 የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ከሊጉ መሪ ሊቨርፑል ጋር መሆኑም የውጤት ቀውሱን እንደሚያባብሰው ይጠበቃል።
በርግጥ ዩናይትድ አሁን ያለበት አቋም ከሊጉ ሊወርድ እንደሚችል የሚያመላክት ነው?
ኤሪክ ቴንሀግን የተኩት ፖርቹጋላዊው ሩበን አሞሪም የማንቸስተር ዩናይትድን የቁልቁለት ጉዞውን ማስቆም እንዳልቻሉ አሃዞች ይጠቁማሉ።
ቀያይ ሰይጣኖቹ በታህሳስ ወር ብቻ ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፈዋል፤ 18 ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል። ይህም ከ1964 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
አሞሪም ዩናይትድን ማሰልጠን ከጀመሩበት ህዳር ወር ወዲህ ከሳውዛምፕተን በመቀጠል ከፍተኛውን የሊግ ሽንፈት አስተናግደዋል። ሳውዛምፕተን ሰባት ጨዋታዎችን ሲሸነፍ ዩናይትድ ስድስት ጊዜ ሽንፈት ቀምሷል።
ዩናይትድ የዘንድሮው የውድድር አጋማሽ 14ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ይህም ከ1989 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በወቅቱ የውድድሩን ዘመኑን ያጠናቀቁት 13ኛ ሆነው እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል።
እነዚህን እና ሌሎች አሃዞችን የሚያነሱ ተንታኞች ማንቸስተር ዩናይትድ ከ50 አመት በኋላ ከሊጉ ሊወርድ እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።