ማርከስ ራሽፎርድ ከማንችስተር ዩናይትድ ሊለቅ የሚችልበት እድል እንዳለ ፍንጭ ሰጠ
የፈረንሳዩ ቡድን ፒኤስጂ ከተጫዋቹ ጋር ተያይዞ በሰፊው ስሙ እየተነሳ ነው
ከእሁዱ የኢትሀድ ድል በኋላ በነገው ዕለት ዩናይትድ በሊግ ካፕ ከቶተንሀም ጋር ይጫወታል
የማንችስተር ዩናይትድ ወጣቱ አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድ ሌሎች ክለቦችን ሊያማትር የሚችልበት እድል እንዳለ ተናግሯል፡፡
ከእግር ኳስ አምደኛው ሄነሪ ዊንተር ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ በዩናይትድ ቤት ቀጣይ ስለሚኖረው ቆይታ ተጠይቆ “ለአዲስ ፈተና ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናግሯል፡፡
የ27 አመቱ እንግሊዛዊ “ሌሎች ተጫዋቾች እንዴት እንደለቀቁ አውቃለሁ እነሱን መሆን አልፈለግም፤ ሁኔታዎች መጥፎ ናቸው ብየ ካሰብኩ ነገሮችን አላባብስም ቡድኑን የምለቅ ከሆነ ስል ዩናይትድ መጥፎ ነገር የምናገርበት አጋጣሚም አይኖርም” ብሏል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት እሁድ በኢትሀድ በተደረገው የማንቹሪያን ደርቢ ጨዋታ ራሽፎርድ እና አርጄንቲናዊው የቡድን አጋሩ አሊሀንድሮ ጋርናቾ ከቡድኑ ተቀነስው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፖርችጋላዊው አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የራሽፎርድን በቡድኑ አለመካታት አስመልክቶ ባደረገው ንግግር የተጨዋቹ መቀነስ ከስነምግባር ጋር እንደማይገናኝ ገልጾ ነበር፡፡
ከቡድኑ ጋር የሚኖረው ቀጣይ ጎዞን በተመለከተ ለቀጣዩ እርምጃ ለቀጣዩ ፈተና ዝግጁ ነኝ ያለው ወጣቱ አጥቂ ቡድኑን የሚለቅ ከሆነ በቅድሚያ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡
ከዩናይትድ ወጣቶች ማሰልጠኛ ወደዋናው ቡድን ከ2016 ጀምሮ የተሸጋገረው እንግሊዛዊ ለቡድኑ በተሰለፈባቸው 426 ጨዋታዎች 138 ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
የ2022/23 የውድድር አመት ለራሽፎርድ ምርጡ የሚባል የውድድር ዘመን ሲሆን በዚህ ጊዜ በሁሉም ውድድሮች 30 ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል፡፡
ነገር ግን ባለፉት 18 ወራት በቀደመው አቋሙ ልክ ግቦችን ማስቆጠር እና ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም የተባለው አጥቂ ከቡድኑ ደጋፊዎች እና ከስፖርቱ ቤተሰብ ጠንካራ ትችትን እያስተናገደ ይገኛል፡፡
በአውሮፓ ዋንጫ በአሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ያልተካተተው ራሽፎርድ በቶማስ ቱህል አዲስ ቡድን ውስጥ ያለው ስፍራም ገና በጥያቄ ውስጥ ይገኛል፡፡
የቢቢሲው የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሞን ስቶን ራሽፎርድ የማንቸስተር ዩናይትድ ህይወቱን በሚመለከት በስሜት መደበላለቅ ውስጥ እንደሚገኝ፤ ከኦልድትራፎርድ የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌለው እና በሩበን አሞሪም አሰላለፍ ውስጥ በቋሚነት ዳግም የመመለስ ብርቱ መሻት እንዳለው ለተጫዋቹ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ነግረውኛል ሲል ዘግቧል፡፡
ሆኖም የጥር ወር የዝውውር መስኮት የራሽፎርድን የኦልትራፎርድ የ8 አመት ቆይታ የሚወስን ይሆናል፡፡
በእርግጥ ከካስሚሮ ባለፈ የቡድኑ ከፍተኛ ተከፋይ የሆነው የ27 አመቱ አጥቂ ከሚጠይቀው ዋጋ አንጻር በርካታ የእንግሊዝ ክለቦች ታጫዋቹን ለማዘዋወር ካላቸው ፍላጎት እንዲገቱ አስገድዷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ግዝያት ከተጫዋቾች ግዥ ርቆ የሰነበተው የፈረንሳዩ ቡድን ፒኤስጂ ከማርከስ ራሽፎርድ ጋር ስሙ በሰፊው እየተያዘ ይገኛል፡፡
የ27 አመቱ እንግሊዛዊ ከዩናይትድ ቤት የሚለቅ ከሆነም ቀጣይ ማረፍያው ፓሪስ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡
በነገው ዕለት ከኢትሀዱ ድል በኋላ የሩበን አሞሪም ቡድን በእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ (ሊግ ካፕ) ከቶተንሀም ጋር ይጫወታል፡፡