“ለማንችስተር ዩናይትድ ትክክለኛው ሰው ነኝ ብየ አስባለሁ”- ሩብን አሞሪም
የ39 አመቱ የዩናይድት አዲስ አሰልጣኝ የመጀመርያ ጨዋታውን በነገው እለት ከኢፕስዊች ጋር ያደርጋል
የሁለት አመት ተኩል ኮንትራት የፈረመው አሞሪም ቡድኑን ለሊጉ ዋንጫ ክብር ለማብቃት ቃል ገብቷል
አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ ዋና አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም ለክለቡ ትክክለኛ ሰው መሆኑን እንደሚያምን ተናገረ፡፡
የ39 አመቱ ተጫዋች በጥቅምት ወር የተሰናበቱትን ኤሪክ ቴን ሃግን በመተካት የሁለት አመት ተኩል ኮንትራት ፈርሟል።
ዩናይትድ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዡ 13ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በ7 ነጥብ ዝቅ ብሎ በ17ተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኝው በዘንድሮው አመት ወደ ሊጉ ካደገው ኢፕኢስዊች ጋር ይገናኛሉ፡፡
ዩናይትድ ለመጨረሻ ጊዜ የሊግ ዋንጫ ካነሳ በኋላ 6ተኛው ቋሚ አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው አሞሪም ለመጀመርያ ጊዜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “በኦልድ ትራፎርድ የሚጠብቀኝን ፈተና ብገነዘብም ክለቡን ማሻሻል እና መለወጥ እንደሚቻል አምናለሁ” ብሏል ፡፡
በተጨማሪም "ከቡድኑ አስተዳደር ጋር አንድ አይነት ሀሳብ ያለን ይመስለኛል ፤ይህ ደግሞ የቡድኑን አቅም ለመጨመር የሚረዳ ነው” ሲል ተናግሯል፡፡
ብዙዎች በተጫዎቹ እምነት እንደሌላቸው ያነሳው አሞሪም በተጨዋቾቹ አቅም እንደሚተማመን እና አዳዲስ ነገሮችን መሞከር እንደሚፈልግ ለዚህ ደግሞ ትክክለኛው ሰው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከአራት አመታት የስፖርቲንግ ሊዝበን ቆይታ በኋላ ዩናይትድን የተቀላቀለው ፖርቹጋላዊ ማንችስተር ዩናይትድን ለዋንጫ ክብር ለማብቃት ጠንክሮ እንደሚሰራም ገልጿል፡፡
“ሊጉ በርካታ ጠንካራ ክለቦች የሚሳተፉበት ቢሆንም ጨዋታዎችን ማሸነፍ እንዳለብን አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሊግ ከባድ ስለሆነ ብዙ ጊዜ እንፈልጋለን። በዚህ ሂደት ውስጥም ወደ ዋንጫ አሸናፊነት የምንቀርብ ይሆናል” ነው ያለው፡፡
3-4-3 ወይም 3-4-2-1 በማጥቃት እና በኳስ ቁጥጥር ላይ ላይ የተመሰረተ ጨዋታ የሚከተለው አሞሪም ወጣቶችን በማብቃት እና አቅማቸውን በማጎልበት ልዩ ችሎታ እንዳለው ይነገርለታል፡፡
ከ2021 ጀምሮ ስፖርቲንግ ሊዝበንን ተረክቦ ማሰልጠን የጀመረ ሲሆን ቡድኑ አምስት ዋንጫዎችን ሲያነሳ በአማካይ 71.7 በመቶ ወይም ከአስር ጨዋታዎች 7 ጨዋታዎችን የማሸነፍ ምጣኔ ያለው ቡድን መገንባትም ችሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ቡድኑ በአማካይ በጨዋታ 2.17 ግቦችን የሚስቆጥር ሲሆን የሚቆጠርበት ግብ 0.18 ብቻ እንደሆነ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡
የእንግሊዝ ፕርሚየር ሊግ ከኢንተርናሽናል ብሬክ በኋላ በዛሬው እለት ማንችስተር ሲቲ ከቶተንሀም ፣ ቼልሲ ከሌስተር ፣ አርሰናል ከኖቲንገሀም ፎረስት ነገ ደግሞ ሳውዝሀምብተን ከሊቨርፑል ፣ እንዲሁም ማንችስተር ዩናይትድ ከ ኢፕስዊች የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡