"ትልቅ ቡድን ስለማሰለጥን ጫናው በዝቶብኛል" - አሞሪም
በፕሪሚየር ሊጉ 14ኛ እና 15 ደረጃ ላይ የሚገኙት ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም ዛሬ ምሽት ይጫወታሉ
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/16/273-160106-ba517bd0-ebf2-11ef-bd1b-d536627785f2_700x400.jpeg)
የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ፖስቴኮግሉ በበኩላቸው አሞሪም ጊዜ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል
በ25ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኙት ማንቸስተር ዩናይትድ እና ቶተንሃም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የሮበን አሞሪሙ ዩናይትድ በ29 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዟል፤ አሰልጣኙ ቡድኑን ከተረከበ በኋላ ካደረጋቸው 20 ጨዋታዎች አስሩን አሸንፎ በስምንቱ ሽንፈት ገጥሞታል።
የአንጅ ፖስቴኮግሉ ቶተንሃም ደግሞ ካለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻለው አራት ነጥብ ብቻ ነው፤ ከሁለት የሀገር ውስጥ ውድድሮች ተሰናብቶ በፕሪሚየር ሊጉም በ27 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ በዚህ የውድድር አመት የተሻለ ፉክክርና ውጤት ያሳየው በማንቸስተር ዩናይትድ ላይ ነው።
ቶተንሃም በመስከረም ወር 2024 በኦልትራፎርድ ዩናይትድን 3 ለ 0 አሸንፏል፤ በካራባዎ ካፕ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታም 4 ለ 3 መርታቱ ይታወሳል።
ስፐርስ ባለፉት አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በማንቸስተር ዩናይትድ አልተሸነፈም (ሁለቱን አሸንፎ በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል)።
"ትልቅ ክለብ ትልቅ ጫና" - አሰልጣኞቹ ስለበረታባቸው ትችት ምን አሉ?
አሞሪም እና ፖስቴኮግሉ ለልዩ የእግርኳስ ፍልስፍናቸው ግትር አቋም የያዙ በሚል ይተቻሉ።
ከጨዋታው በፊት አሰልጣኞቹ አንዱ ስለሌላው ሲጠየቁ ግን የሚቀርብባቸውን ትችት ተከላክለው አድናቆት ተለዋውጠዋል።
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ሮበን አሞሪም የአውስትራሊያው አሰልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ "ቀንደኛ አድናቂ" መሆኑን ተናግሯል። ፖስቴኮግሉ "እግርኳስን በትክክለኛው መንገድ ለመጫወት የሚመርጥ" ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ውጤት ብቻ በሚጠብቁ ደጋፊዎች የሚደርስበትን ጫናም እረዳዋለሁ ነው ያለው።
"ውጤት እየቀናን ባለመሆኑ ተመሳሳይ ችግር አለብን፤ ነገር ግን እኔ ትልቅ ቡድን ስለማሰለጥን ትልቅ ጫና አለብኝ" ሲልም አክሏል።
የቶተንሃሙ አሰልጣኝ አንጅ ፖስቴኮግሉ በበኩላቸው ዩናይትድ አሞሪምን ቢያንስ ለሁለት አመት ቢታገሰው ውጤት እንደሚያመጣ ገልጸዋል።
"የምንዳኘው በውጤት ነው ይገባኛል፤ እናንተ በእኔ ወይም በአሞሪም ቦታ ብትሆኑ ትረዱን ነበር፤ ውጤት ራቀ ማለት በሚገባ እያሰለጠናችሁ ማለት አይደለም" በሚልም ትችቶችን ተከላክለዋል።
ዩናይትድ ከ14ኛ፤ ቶተንሃም ደግሞ ከ15ኛ ደረጃቸውን ወደ 12ኛ ከፍ ለማድረግ የሚያደርጉት ጨዋታ የወትሮው ተጠባቂነት ባይኖረውም በአሰልጣኞቹ ላይ የበረታውን ትችት ለማለዘብ እንደሚያግዝ ይታመናል።
በሌላ የ25ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር መሪው ሊቨርፑል በአንፊልድ ወልቭስን 11 ስአት ላይ ይገጥማል።