የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ቴል አቪቭ ገቡ
ሚኒስትሩ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር ከፍተኛ ውግዘት በደረሰበት የትራምፕ የጋዛ እቅድ ዙሪያ እንደሚመክሩ ይጠበቃል

ሩቢዮ በአከራካሪው እቅድ ዙሪያ ለመምከር ወደ ሳኡዲ አረቢያ እና አረብ ኤምሬትስም ያቀናሉ
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በመካከለኛው ምስራቅ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ለማድረግ እስራኤል ገብተዋል።
በሙኒክ የደህንነት ጉባኤ ተሳትፈው ወደ ቴል አቪቭ ያቀኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዛሬ በእየሩሳሌም ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ይመክራሉ።
የውይይታቸው ዋነኛ አጀንዳም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትና ከፍተኛ ውግዘት የደረሰበት ጋዛን የመጠቅለል እቅድ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በቅርቡ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት ኔታንያሁ የትራምፕን የጋዛ እቅድ እንደሚደግፉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው "እስራኤል በቀጣይ ምን እንደምታደርግ (በጋዛ ጉዳይ) የምትወስነው አሁን ነው፤ አሜሪካ የእስራኤልን ውሳኔ ትደግፋለች" ብለዋል።
ሩቢዮ ቴል አቪቭ የገቡት ሃማስ እና እስራኤል የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ አድርገው የጋዛ ተኩስ አቁም ከተጋረጠበት የመፍረስ አደጋ ከዳነ ከስአታት በኋላ ነው።
ትራምፕ የፍልስጤሙ ቡድን ሁሉንም ታጋቾች እስከ ትናንት ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ካልለቀቀ "ከፍተኛ ትርምስ" ይፈጠራል በሚል ቢያስጠነቅቁም የታጋቾችና እስረኞች ልውውጡ ተካሂዷል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ መፍረስ ለትራምፕ ጋዛን የመጠቅለል እቅድ ጥሩ እድል ይፈጥራል ተብሎ ቢገመትም ለጊዜውም ቢሆን ሳይሳካ ቀርቷል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኔታንያሁ ጋር የሚያደርጉት ምክክር ፍልስጤማውያንን ከጋዛ አስወጥቶ ጋዛን "የመካከለኛው ምስራቅ ሪቬራ" የማድረግ እቅድን ማሳካት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሬውተርስ ዘግቧል።
የመጀመሪያው ምዕራፍ የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት ብቻ የቀረው በመሆኑም በሁለተኛው ምዕራፍ ስምምነት ዙሪያ ድርድር በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ይወያያሉ ተብሏል።
ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች በሁለተኛው ምዕራፍ የታጋቾች እና እስረኞች ልውውጥ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር በቀጣዩ ሳምንት በዶሃ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
ሩቢዮ የቴል አቪቭ ቆይታቸውን ሲያጠናቅቁ ወደ ሳኡዲ አረቢያ እና አረብ ኤምሬትስ ያቀናሉ።
ሪያድ እና ሌሎች የአረብ ሀገራት የትራምፕን ፍልስጤማውያንን ከጋዛ የማፈናቀል እቅድ ማውገዛቸው የሚታወስ ነው።