የኡጋንዳው ጀነራል በዴሞክራቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ ላይ ጥቃት ለመክፈት ዛቱ
የፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ልጅ ጀነራል ሙሆዚ ካይነሩጋባ በምስራቃዊ ኮንጎ ቡኒያ ከተማ "ሁሉም የታጠቁ ሃይሎች" በ24 ስአት ውስጥ ትጥቅ እንዲፈቱ አሳስበዋል

ጀነራሉ በኤክስ ገጻቸው ላይ አነጋጋሪ "የወረራ ዛቻ" መልዕክቶችን በማስፈር ይታወቃሉ
የኡጋንዳ ጦር አዛዡ ጀነራል ሙሆዚ ካይነሩጋባ በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጥቃት ለመክፈት ዝተዋል።
ጀነራሉ በጎረቤት ኮንጎ ቡኒያ ከተማ የሚገኙ ሁሉም የታጠቁ ሃይሎች" በ24 ስአት ውስጥ ትጥቅ እንዲፈቱ በኤክስ ገጻቸው ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በምስራቃዊ ኮንጎ የሚኖሩ የባሂማ ጎሳ አባላት በታጠቁ አካላት እየተገደሉ መሆኑን አንስተዋል።
"የኔ ህዝብ ባሂማ ጥቃት እየደረሰበት ነው፤ በህዝቤ ላይ ጥቃት የሚከፍቱ አካላት በጣም አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸው ማወቅ አለባቸው፤ በዚህ ምድር የትኛውም ሃይል ህዝቤን መግደል አይችልም" ሲሉም ጥቃቱ ካልቆመ ጦራቸውን እንደሚያዘምቱ አስጠንቅቀዋል።
"ቡኒያ በቅርቡ በኡጋንዳ ጦር ስር ትገባለች" ሲሉም ነው የገለጹት።
ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ (አባታቸው) በቦኒያ የኡጋንዳን ጦር አሰማርተው የባሂማ ጎሳ አባላትን እንዲጠብቁ ፈቃድ እንደሰጧቸውም አብራርተዋል።
የኡጋንዳ ጦር ቃልአቀባይ በጀነራሉ መልዕክት ዙሪያ ምላሽ ለመስጠት ተጠይቀው ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ሬውተርስ በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙትን የዲአር ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩዲት ሱሚንዋ አስተያየትን ጠይቆ "ምንም ማለት አልችልም" የሚል ምላሽ አግኝቷል።
የሙሴቬኒን በትረ ስልጣን እንደሚረከቡ የሚጠበቁት ጀነራል ሙሆዚ ካይነሩጋባ ማስጠንቀቂያ በኮንጎ እና ሩዋንዳ ትደግፋቸዋለች በሚባሉት የ"ኤም23" አማጺያን መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ቀጠናዊ መልክ እንዲይዝ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የኤም23 መሪ ከትናንት በስቲያ አማጺያኑ በምስራቃዊ ዲአር ኮንጎ ሁለተኛ ግዙፍ ከተማ ወደሆነችው ቡካቩ ከተማ መግባታቸውን ይፋ አድርገዋል። አማጺያኑ ባለፈው ወር ትልቋን ከተማ ጎማ በቁጥጥር ስር ማዋላቸው የሚታወስ ነው።
ሬውተርስ የመንግስታቱ ድርጅት ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ኡጋንዳ ሽብርተኞችን ለመዋጋት በሚል ተጨማሪ ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮችን ወደ ምስራቃዊ ኮንጎ ልካለች።
ኪጋሊ ቱትሲ መራሹን "ኤም23" አማጺ ቡድን እንደምትደግፍና ወታደሮቿ ከአማጺያኑ ጎን ተሰልፈው እንደሚዋጉ ወቀሳ ይቀርብባታል። የፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ አስተዳደር ግን ወቀሳውን ሲያስተባብል ይደመጣል።
የኡጋንዳው ጀነራል ሙሆዚ ካይነሩጋባ ለሩዋንዳው ፕሬዝዳንት እና ለ"ኤም23" ደጋግሞ ድጋፉን ገልጿል። ጀነራሉ በ2022 አማጺያኑን "የቱትሲዎች መብት በኮንጎ እንዲከበር የሚዋጉ ወንድሞቻችን ናቸው" ብለዋቸው ነበር።
የትናንቱ የማስጠንቀቂያ መልዕክትም ኡጋንዳ በዲአር ኮንጎ ኢቱሪ ግዛት ኢኮኖሚያዊ እና ጂኦፖለቲካዊ ፍላጎት እንዳላት ለመግለጽ ያለመ መሆኑን ተንታኞች አንስተዋል።
አወዛጋቢ አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት ካይነሩጋባ በ2022 ጎረቤት ኬንያን እንደሚወሩ መዛታቸው የሚታወስ ነው።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዮጂያ ሜሎኒ የጋብቻ ጥያቄየን ካልተቀበለች "ጣሊያንን እወራለሁ" ማለታቸውም መነጋገሪያ እንደነበር አይዘነጋም።