በቀድሞው የዩናይትድ አምበል ሩኒ “ሞኝ” ተብሎ የተዘለፈው ሩብን አሞሪም ምን ምላሽ ሰጠ?
እንግሊዛዊው ዋይኒ ሩኒ “አሞሪም ከፊቱ ያለውን ጨዋታ ሳያሸንፍ ስለ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊነት ማውራቱ ሞኝነት ነው” ሲል ተናግሯል

በሩበን አሞሪም ስር ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 10ኛ ሽንፈቱን ትናንት ያስተናገደው ዩናይትድ ከኤፍኤ ካፕ ዋንጫ ፉክክር ውጭ ሆኗል
የማንቸስተር ዩናይትዱ ዋና አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የክለቡ አላማ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት እንደሆነ መናገሩን ተከትሎ በቀድሞው የክለቡ አምበል ዋይኒ ሩኒ “ሞኝ” ከተባለ በኋላ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አሞሪም ከፉልሀም ሽንፈት በኋላ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የክለቡ ዋነኛ አላማ ከቀድሞው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ማሳካት ነው ሲሉ ተናግሮ ነበር፡፡
አሰልጣኙ በንግግሩ "በጨዋታዎች እንደምንሸነፍ አውቃለሁ፤ ነገር ግን አላማችን ፕሪሚየር ሊጉን እንደገና ማሸነፍ ነው፤ ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ አላውቅም፤ አላማ አለን ስለዚህ ምንም ቢሆን ወደፊት እንቀጥላለን" ብሏል፡፡
ለዚህ ንግግር አስተያየት የሰጠው ዋይኒ ሩኒ “አሞሪም በስራው መቆየት የሚፈልግ ከሆነ የአጭር ጊዜ እቅዶች ላይ ማተኮር ይገበዋል” ሲል ተናግሯል፡፡
“ፕሪምየር ሊጉን ማሸነፍ እፈልጋለሁ ብሎ መናገር ትንሽ ሞኝነት ይመስለኛል፤ ምክንያቱም አሁን ክለቡ የሚገኝበት አቋም ከዋንጫው ፉክክር በጣም ሩቅ ነው” ብሏል ሩኒ፡፡
አሞሪም ማንችስተር ዩናይትድ በአሰልጣኝነት ከተረከበ ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ ከሚያሳየው አቋም የተሻለ ውጤት እንደሚያስፈልገው የገለጸው ሩኒ፤ ስለ ዋንጫ ባለቤትነት ከመወራቱ በፊት በደረጃ ሰንጠረዡ የሚገኝበትን ደረጃ ማሻሻል ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ነው የተናገረው፡፡
አሰልጣኙ ለቀድሞው የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና አምበል ዋይኒ ሩኒ በሰጠው ምላሽ “ስለ ክለቦች ማውራት እና ማሰልጠን የተለያዩ ነገሮች ናቸው” ብሏል፡፡
“የሊጉን ዋንጫ አናሸንፋለን ስል በዛሬው ዕለት አደርገዋለሁ እያልኩ እንዳልሆነ ሁሉም ሰው ይረዳል ብየ አስባለሁ፤ ክለቡ የዋንጫ አሸናፊ እና ብርቱ ተፎካካሪ ሆኖ የሚቀርብበትን አቅም መገንባት አላማ ይዤ እየሰራሁ ነው” ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ዩናይትድ በአሞሪም መሪነት በ24 ጨዋታዎች 10ኛውን ሽንፈት ትላንት አስተናግዷል፤ በአምስተኛው ዙር የኤፍኤ ካፕ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያ በፉልሃም በፍጹም ቅጣት ምት ተሸንፎ ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በህዳር ወር ቡድኑን ከተረከበ በኋላ በኦልትራፎርድ 6ተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደ ሲሆን፤ በሚቀጥለው አመት በአውሮፓ የውድድር መድረኮች ላይ ለመሳተፍ የኢሮፓ ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡