ሩብን አሞሪም ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ የከፋ አፈጻጸም ያላቸው አሰልጣኝ መሆናቸው ተነገረ
አሰልጣኙ በ14 ጨዋታዎች ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ከቀድሞው 6 አሰልጣኞች አንጻር ሲወዳደር ዝቅተኛው ነው

በአሁኑ ወቅት በፕሪምየር ሊጉ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝው ዩናይትድ በመጪው ቅዳሜ ኤቨርተንን ይገጥማል
ኔዘርላንዳዊውን አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ ተክተው ከፖርቹጋል ወደ ኦልትራፎርድ ያቀኑት ሩብን አሞሪም ጥሩ አጀማመር እንዳስመዘገቡ እየተነገረ ነው፡፡
የሩበን አሞሪም የመጀመሪያዎቹ 14 የማንችስተር ዩናይትድ ግጥሚያዎች ከስድስት የኦልድትራፎርድ ቀደምት አሰልጣኞች ጋር ሲነፃፀር ደካማው ውጤት ሆኗል፡፡
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከለቀቁ ከ12 አመታት በኋላ የሩበን አሞሪምን ያህል ደካማ ውጤት ያስመዘገበ አሰልጣኝ የለም፡፡
የአሞሪም የጨዋታ ስትራቴጂ ገና መሬት ባልረገጠበት ሁኔታ ቡድኑ በሜዳው እና ከሜዳው ውጭ ተደጋጋሚ ሽንፈቶችን እስተናገደ ነው፡፡
ቀያይ ሰይጣኖቹ ከኢፕስዊች ጋር አቻ ከተለያዩ እና ኤቨርተንን ካሸነፉ በኋላ ካደረጓቸው 12 ጨዋታዎች ስምንቱን ተሸንፈዋል፡፡
አሞሪም በዚህ ጉዞ ውስጥ በማንችስተር ሲቲ ላይ የተቀዳጁት ድል ከሳውዝሀምብተን እና ከፉልሀም ጋር ያስመዘገቡት ድል ተጠቃሽ ቢሆንም በአጠቃላይ ጨዋታዎች ያስመዘገቡት ውጤት ከቀድሞ አስልጣኖች ጋር ሲነጻጸር በዝቅተኛነቱ ቀዳሚ ሆኗል፡፡
ከአሞሪም በፊት በኦልትራፎርድ በ14 ጨዋታዎች ዝቅተኛ ውጤት በማስመዝገብ መጥፎ ታሪክ ያላቸው ጆሴ ሞሪኒሆ ሲሆኑ አሰልጣኙ በ14 ጨዋታዎች የሰበሰቡት ነጥብ 21 ብቻ ነበር፡፡
በ2016 አሰልጣኝነቱን የተረከቡት ሞሪኒሆ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ጨዋታዎች ካሸነፉ በኋላ ተከታታይ ሽንፈቶችን አስተናግደዋል።
የቀድሞው የቼልሲ አለቃ በአቻ ውጤት እና በሽንፈት ያስተናገዷቸው ውጤቶች መበራከት በቡድኑ የመጀመሪያ አመት የነበራቸውን ቆይታ አክብዶባቸዋል፡፡
ከሞሪኒሆ በመቀጠል በኦልትራፎርድ የመጀመሪያ ጨዋታወች ጥሩ ታሪክ ከሌላቸው አሰልጣኞች መካከል ሌላኛው ስኮትላንዳዊው ዴቪድ ሞይስ ሲሆኑ አሰልጣኙ በ14 ጨዋታዎች መሰብሰብ የቻሉት 22 ነጥብ ብቻ ነው፡፡
ልዊስ ቫንሀል 25 ነጥብ ፣ ኤሪክ ቴንሀግ ፣ 26 ነጥብ ፣ ራልፍ ራንኒክ 26 ፣ ኦሊጎነር ሶልሻየር 35 ነጥብ በማስመዝገብ ከአሌክስ ፈርጉሰን በኋላ የተተካኩት አሰልጣኞች በደረጃ ተቀምጠዋል
ኔዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ኤሪክ ቴንሀግ አጨራረሱ ጥሩ ባይሆንም ጅማሮው ላይ የተሻሉ የጨዋታ እንቅስቃሴዎችን በማሳያት ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
የቴንሀግ ውጤት ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን ቀጥሎም በ14 ጨዋታዎች የተመዘገበ ሁለተኛው ከፍተኛው ውጤት ነው፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ ከሚገኝበት የውጤት ቀውስ ያወጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት አሞሪም አጀማመሩ በሽንፈት የታጀበ ሆኗል፡፡
የተለየ የጨዋታ አሰላለፍን እና ስትራቴጅን ለመፍጠር ጥረት ላይ በሚገኝው አሰልጣኝ የሚመራው ቡድን በአሁኑ ወቅት በ15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ፡፡