የክርስቲያኖ ሮናልዶ የግል አውሮፕላን በእንግሊዝ ማንችስተር እንዲያርፍ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?
76 ሚሊየን ዶላር ዋጋ የሚያወጣው ቦምባርድኤር አውሮፕላን ባሳለፍነው አርብ በማንችስተር ኤርፖርት ከቆመበት እስካሁን አልተንቀሳቀሰም

የእንግሊዝ ጋዜጦች የአውሮፕላኑን መታየት ተከትሎ የተለያዩ ሀሳቦችን እያነሱ ሲዘግቡ ሰንብተዋል
የፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የግል አውሮፕላን በእንግሊዝ ማንችስተር ኤርፖርት መታየቱ ለውዝግብ ምንጭ ሆኗል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በማንችስተር ከታየው አውሮፕላን ጉዳይ ጀርባ የተለያየ አጀንዳዎችን በመምዘዝ የእንግሊዝ ጋዜጦች ሲዘግቡ ከርመዋል፡፡
አንዳንድ የዩናይትድ ደጋፊዎች የ40 አመቱ የቀድሞ የክለቡ ኮከብ በአስገራሚ ሁኔታ ወደ ኦልድትራፎርድ ሊመለስ እንደሚችል እንዲገምቱ አድርጓቸዋል፡፡
በ25 የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች 28 ጎሎችን በማስቆጠር በግብ እና አሸናፊነት ድርቅ የተመቱት ቀያይ ሰይጣኖቹ በሊጉ 15ኛ ደረጃ ላይ በሚገኙበት ወቅት የቀድሞ የጎል ማሽን ተጫዋቻቸውን መመለስ ቢመኙ አያስደንቅም ሲል ጎል ዶትኮም አስነብቧል፡፡
የእንግሊዙ ዘ ሰን ጋዜጣ ዛሬ ይዞት በወጣው ዘገባ የአውሮፕላኑ በማንችስተር መታየት ከማንችስተር ዩናይትድ እግር ኳስ ቡድን ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አስነብቧል፡፡
ይልቁንም አውሮፕላኑ በማንችስተር ለማረፍ የተገደደው በመስኮቱ ላይ ባጋጠመው ድንገተኛ መሰንጠቅ እንደሆነ ጋዜጣው ዘግቧል፡፡
“ቦምባርድኤር ግሎባል ኤክስፕረስ 6500” የተሰኘው 76 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣው አውሮፕላን ያጋጠመውን የቴክኒክ ችግር ለመቅረፍ የሚቀየሩ እቃዎች እስኪደርሱ ድረስ አሁንም በማንችስተር ኤር ፖርት ይገኛል ነው የተባለው፡፡
እንደዘገባው ከሆነ አልናስር አልሂላልን 3-2 ባሸነፈበት ጨዋታ ተሰልፎ የነበረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአርቡ በረራ ላይ አውሮፕላኑ ውስጥ አልነበረም፡፡
ሮናልዶ “ገልፍስትሪም ጂ 200” የተባለውን የመጀመሪያ አውሮፕላኑን በ20 ሚሊየን ዩሮ ከገዛ በኋላ ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ የገዛው ይህ አውሮፕላን አለም አቀፋዊ መታወቂያው ሲአር 7 (cr7) እና ግብ ሲስቆጥር ደስታውን የሚገልጽበት ሱ…. ("Suiii") የተባለው ቃል ተጽፎበታል ፡፡
በ2003 ዩናይትድን የተቀላቀለው ሮናልዶ ለክለቡ ባደረጋቸው 346 ጨዋታዎች 145 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን በአሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ስር ውጤታማ ከነበሩ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡