የቀድሞ የአርሰናል እና ሪያል ማድሪድ አማካይ ሜሱት ኦዚል የቱርክን ፖለቲካ ተቀላቀለ
የ36 አመቱ የቀድሞ የእግር ኳስ ኮከብ የቱርኩን ገዢ ፓርቲ መቀላቀሉ ታውቋል

የቱርክ ዝርያ እንዳለው የሚነገርለት ኦዚል ከፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን ጋር ባለው ግንኙነት ሲተች ቆይቷል
ቀድሞ የአርሰናል እና ሪያል ማድሪድ አማካይ ሜሱት ኦዚል የቱርክን ፖለቲካ መቀላቀሉ ተነገረ፡፡
ኦዚል የቱርክ ገዢ ኤኪ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ፓርቲውን መቀላቀሉን እና የፓርቲው አባል መሆኑ በይፋ ተገልጿል፡፡
በ2018 ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን ራሱን ያገለለው እግር ኳስ ተጫዋቹ ጡረታ ከመውጣቱ ከአምስት አመታት በፊት ከቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶሀን ጋር በለንደን መገናኘቱ ከፍተኛ ውዝግብን አስከትሎበት ነበር፡፡
የቱርክ ዘር ሀረግ እንዳለው የሚነገርለት ኦዚል ከዚህ ጊዜ በኋላ ከኤርዶሀን ጋር አላቸው በሚባለው የጠበቀ ግንኙነት በጀርመን ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች እና በሌሎች አውሮፓውን ትችትን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡
በወቅቱ የጀርመን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ የነበሩት ሬይንሃርድ ግሪንደል ተጫዋቾቹ ለኤርዶሀን ፖለቲካዊ ዓላማ መጠቀሚያ እንዲሆን ፈቅዷል ሲሉ ከሰውታል።
አንዳንድ የጀርመን ፖለቲከኞች ኦዚል ለጀርመን ያለውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ከ2018 የአለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ እንዲገለልም ጠይቀው ነበር፡፡
ተጫዋቹ ከአለም አቀፍ እግር ኳስ ራሱን ማግለሉን ባሳወቀበት መልዕክት ከኤርዶሀን ጋር የተነሱት ፎቱ ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው እና ለቤተሰቦቹ ሀገር መሪ ካለው ክብር አንጻር የተነሳው ፎቶ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡
ከዚህ ውዝግብ በኋላ በኢስታንቡል ከቱርካዊት ባለቤቱ አሚኒ ጉልሲ ጋር ባደረገው የጋብቻ ስነ ስርዐት ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ታድመው ነበር፡፡
ከ2003 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ከ2014 ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት በስልጣን ላይ የቆዩት ኤርዶሀን ቱርክን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መርተዋል ፡፡
በ2014 ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን ጋር የአለም ዋንጫን ያሸነፈው ኦዚል በ2021 አርሰናልን ለቆ ወደ ቱርኩ ፌነርባቼ ከገባ በኋላ በ2022 ወደ ኢስታንቡል ባሳክሴሂር በማቅናት ከአንድ አመት በኋላ ከእግር ኳስ ራሱን አግልሏል፡፡
ኦዚል በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ለአርሰናል ተሰልፎ በተጫወተባቸው 184 ጨዋታዎች 33 ግቦችን እና 56 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ማቀበል ችሏል፡፡