ወደ ጠፈር ለመጓዝ 60 ዓመታትን የጠበቁት አዛውንት ሊጓዙ ነው
ዋሊ ፈንክ በ1960ዎቹ መባቻ የናሳ መስፈርቶችን አሟልተው በግል ለጠፈርተኛነት ከሰለጠኑ 13 ሴት አስትሮኖቶች (Mercury 13) መካከል አንዷ ናቸው
አዛውንቷ ከቁጥር አንዱ የዓለማችን ቱጃር ጄፍ ቤዞስ ጋር ነው ወደ ጠፈር የሚጓዙት
ወደ ጠፈር ለመጓዝ 60 ዓመታትን የጠበቁት የ82 አመቷ አዛውንት ዋሊ ፈንክ በያዝነው ወር እኩሌታ ወደ ጠፈር ሊጓዙ ነው፡፡
አዛውንቷ ከቁጥር አንዱ የዓለማችን ቱጃር ጄፍ ቤዞስ ጋር ነው ወደ ጠፈር የሚጓዙት፡፡
ብሉ ኦርጂን የተሰኘው የቱጃሩ ቤዞስ የጠፈር ጉዞዎች ኩባንያ በመጪው ሃምሌ 20 (እ.ኤ.አ) ኒው ሼፈርድ የተሰኘች መንኮራኩርን ያስወነጭፋል፡፡
ጉዞው አራት ሰዎችን የሚያሳትፍ ሲሆን ማርክ የተባለው የቤዞስ ወንድም እና አንድ የጉዞውን ጨረታ በ28 ሚሊዬን ዶላር ያሸነፈ ግለሰብ የጉዞው አካል ይሆናሉ ተብሏል፡፡
አዛውንቷ ዋሊ ፈንክ በ1960ዎቹ መባቻ የአሜሪካ የህዋ ምርምር ተቋም (ናሳ) መስፈርቶችን አሟልተው በግል ለጠፈርተኛነት ከሰለጠኑ 13 ሴት አስትሮኖቶች (Mercury 13) መካከል አንዷ ናቸው፡፡
ሆኖም አንደኞቹም የMercury 13 ሰልጣኞች ወደ ጠፈር ሳይጓዙ ቀርተዋል፡፡ ይህ በሴትነታቸው ምክንያት የሆነ እንደሆነም ነው ዋሊ የተናገሩት፡፡
ምናልባትም ውጥኑ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ወደ ጠፈር ለመጓዝ የቻሉ የመጀመሪያዎቹ ሴት ጠፈርተኞች ይሆኑ ነበር፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሚደረገው ጉዞ የሚሳካ ከሆነ ዋሊ ወደ ጠፈር ለመጓዝ የቻሉ የመጀመሪያዋ አዛውንት ይሆናሉ፡፡
የእድሜ ክብረ ወሰኑ በ77 ዓመቱ ወደ ጠፈር በተጓዘው አሜሪካዊው አስትሮኖት ጆን ግሌን የተያዘ ነበር፡፡