የ30 ኒኩሌር ቦምብ አቅም ያለው አስትሮይድ ወደ ምድር እየተጠጋ ነው ተባለ
ናሳ በበኩሉ በ2022 የመጀመሪያ ወር ላይ አምስት አስትሮይዶች ወደ ምድር እየተጠጉ ነው ብሏል
አስትሮይዱ በፈረንጆቹ በሚያዚያ ወር 2029 ከምድር ጋር የመላተም እድል ሊኖረው ይችላል ተብሏል
የሩሲያ የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴር አስትሮይድ (የጠፈር አለት) በጣም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ወደ ምድር እቅጣጫ እየተጓዘ መሆኑን አስታውቋል።
የመላው ሩሲያውያን የዚቪል ጥናት ኢኒስቲትዩት በበኩሉ “አፖፊዚስ” የሚል መጠሪያ ያለው አስትሮይድ ከ7 ዓመታት በኋላ ማለትም በፈረንጆቹ በሚያዚያ ወር 2029 ከምድር ጋር የመላተም እድል ሊኖረው ይችላል ብሏል።
አስትሮይዱ ከምድር ጋር የሚጋጭ ከሆነ 1 ሺህ 717 ሜጋ ቶን ኃይል ሊፈጠር እንደሚችልም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
በግጭቱ ምክንያት የሚፈጠረው ኃይልም ጉዙፉ የተባለው የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ቴርሞኒኩሌር በፈነዳበት ጊዜ ከፈጠረው ኃይል በ30 እጥፍ የሚበልጥ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
አስትሮይድ በሚወድቅበት ስፍራ እና በአካባቢው በሚገኙ 10 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ርእደ መሬት ሊፈጠር ይችላል የተባለ ሲሆን፤ ንዝረቱም በሰከንድ በ790 ሜትር ፍጥነት በርከታ ስፍራዎች ላይ ሊሰማ እንደሚችልም አስታውቀዋል።
የአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም ናሳ በበኩሉ በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 የመጀመሪያ ወር ላይ አምስት አስትሮይዶች ወደ ምድር እየተጠጉ ነው ሲል አስታውቋል።
ከእነዚህም ውስጥ በያዝነው ሳምንት ብቻ የአውቶብስ መጠን ያለው አንድ አስትሮይድ ለምድር በጣም ሊቀርብ እንደሚችልም ናሳ አስታውቋል።
በመገባደድ ላይ ባለው የታህሳስ ወር በፈረንሳይ ፓሪስ የሚገኘውን የኢፍል ታወር የሚያህል 330 ሜትር ርዝመት ያለው አስትሮይድ ምድርን ስቶ ማለፉ ተነግሯል።
የናሳ የምድር አቅራቢያ የነገር ጥናት ማዕከል መረጃ እንደሚያመለክተው በፈረንጆቹ ከ1990 ጀምሮ 26 ሺህ 115 አስትሮይዶች ምድርን ለመግጨት ቃጥተው ነበር ብሏል።
አስትሮይድ ምንድነ ነው?
አስትሮይዶች (የጠፈር አለት) በአብዛኛዎቹ የጠፈር መስክ ምሁራን ከፕላኔቶች መፈጠር በኋላ የመጡ ግኡዛን ቅሪቶች ናቸው ተብሎ ይታመናል።
አስትሮይድ ከፕላኔቶች በተለየ መልኩ ያልተስተካከለ ቅርፅ ያላቸው ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜ ጥቃቅን ፕላኔቶች ተብለው ይጠራሉ።የፀሐይ ጨረር የሚያንፀባርቁ እንደ ጨረቃ ያሉ ቀዝቃዛ ነገሮች መሆናቸውም ይነገራል።
በየቀኑ ከ100 ቶን የሚበልጥ ከአስትሮይድና ከኮሜት አፈትልከው የሚወጡ ግኡዛን ወደ ምድር አቅጣጫ የሚመጡ ቢሆኑም ነገር ግን ወደ ምድር ከባቢ አየር ሲገቡ በብናኝ መልክ ይጠፋሉ።