በሚሳዔሉ የተመታቸው ሳተላይት ስብርባሪ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ውስጥ ያሉ ጠፈርተኞች ስራ አስተጓጉሏል
ሩሲያ የፀረ ሳታላይት ሚሳዔል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራንት ማስቆጣቱ ተሰምቷል።
ሩሲያ ዛሬ አካሂዳለች በተባለው የፀረ ሳታላይት ሚሳዔል ሙከራ በጠፈር ላይ ከሏት ሳተላይቶች አንዱን ማፈንዳቷ ታውቋል።
ይህንን ተከትሎ የሳተላይቷ ስብርባሪ በዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ (አይ.ኤስኤስ) ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞችን አደጋ ላይ ጥሏል የተባለ ሲሆን፤የጣቢያው ሠራተኞችም ወደ መጠለያ ካፕሱላቸው እንደገቡ አድርጓል ነው የተባለው።
በሙከራው ስራው ተስተጓጉሏል የተባለው የዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ ውስጥ 7 ጠፈርተኞች ያሉ ሲሆን፤ ከጠፈርተኞቹ ውስጥ አራቱ የአሜሪካ፤ ሁለት የሩሲያ እና አንድ የጀርመን ዜጎች መሆናቸውም ተነግሯል።
አሜሪካ የሩሲያን ሙከራ ተከትሎ በሰጠችው መግለጫ፤ ሩሲያ “በግዴለሸነት” ባደረገችው የፀረ ሳታላይት ሚሳዔል ሙከራ እስካሁን ድረስ በርካታ ስብርባሪዎች በፍጠሩን በመጥቀስ፤ ተግባሩ የሁሉንም ሀገራት ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብላለች።
የአሜሪካው የጠፈር ተቋም ናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰንም በሩሲያ የፀረ ሳታላይት ሚሳዔል ሙከራ መናደዳቸው አስታውቀዋል።
የብሪታኒያ የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስም በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የሩሲያን ተግባር ያወገዙ ሲሆን፤ ሙከራው "የጠፈር ደህንነት ችላ መባሉን ያሳያል" ብለዋል።
የሩሲያው የጠፈር ተቋም በበኩሉ ነገሩን ያቀለለው ሲሆን፤ ስብርባሪው ከዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ መራቁን እና ጣቢያው በአረንጓዴ ዞን ውስጥ መግባንቱን በትዊተር ገጹ ባወጣው መረጃ አመላክቷል።