ጃፓናዊው ቢሊየነር የ12 ቀናት የጠፈር ቆይታውን አጠናቆ ተመለሰ
ስፔስ ኤክስ የተሰኘው የኤሎን መስክ ኩባንያ በ2023 ወደ ጨረቃ ለሚያደርገው ጉዞ ከወዲሁ ለመዘጋጀት በማሰብ ነው ቢሊዮኔሩ ወደ ጠፈር የተጓዘው
ዩሳኩ ማዔዛዋ የጠፈር ቆይታውን አጠናቆ ዛሬ ሰኞ ወደ ምድር ተመልሷል
ጃፓናዊው ቢሊየነር የ12 ቀናት የጠፈር ቆይታውን አጠናቆ ወደ ምድር ተመለሰ፡፡
ታዋቂው የፋሽን ባለሙያ ዩሳኩ ማዔዛዋ ከፋሽን ዲዛይነሩ ዮዞ ሂራኖ እና ከሩሲያዊው ጠፈርተኛ አሌክሳንደር ሚሱርኪን ጋር በመሆን ነበር በሩሲያ ሰራሹ ሶዩዝ መንኮራኩር ወደ ዓለም የጠፈር ማዕከል (International Space Station) ያቀኑት፡፡
በዚያም የነበራቸውን የ12 ቀናት ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ሰኞ በሰላም ወደ ምድር ተመልሰዋል፡፡
ሶስቱን የጠፈር ተጓዦች የያዘችው መንኮራኩር ዛሬ ሊረፋፍድ አካባቢ በተራራማ የደቡባዊ ካዛኪስታን አካባቢዎች አርፋለች፡፡
ወደ ጠፈር ለመጓዝ 60 ዓመታትን የጠበቁት አዛውንት ሊጓዙ ነው
ሩሲያ በዚህ ስፍራ በሊዝ ተከራይታ የገነባችው እና ከ1950ዎቹ ጀምሮ የምትጠቀመው የመንኮራኩር እና ሮኬቶች ማስወንጨፊያ ስፍራ አላት፡፡
ቢሊዮኔሩ ጃፓናዊ የፋሽን ቱጃር የጠፈር ጉዞውን ያደረገው ከዚሁ ማዕከል በመነሳትም ነው፡፡
የ46 ዓመቱ ዩሳኩ ማዔዛዋ እና የ36 ዓመቱ ዮዞ ሂራኖ በራሳቸው ወጪ ነው የጠፈር ማዕከሉን ጎብኝተው የተመለሱት፡፡ ምን ያህል እንደከፈሉ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ሆኖም በተናጠል እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ሳይከፍሉ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ ዩሳኮ የ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ነው፡፡
‘ስፔስ ኤክስ’ የተሰኘው የኤሎን መስክ ኩባንያ በ2023 ወደ ጨረቃ ለሚያደርገው ጉዞ ከወዲሁ ለመዘጋጀት በማሰብ ነው ቢሊዮኔሩ ወደ ጠፈር የተጓዘው፡፡
ለጥቂት ደቂቃዎች ወደ ጠፈር ለመጓዝ የአንድ ወንበር የጨረታ ዋጋ ከ2 ነጥበ 4 ሚሊዮን ዶላር አለፈ
ከሳምንት በፊት ስለ ጠፈር ጉዞውና ቆይታው በአሶሼትድ ፕሬስ የተጠቀው ቱጃሩ ጃፓናዊ እጅግ አስደሳች እንደሆነ ነገር ግን ከመሬት ስበት ዜሮ መሆን ጋር በተያያዘ ስላጋጠሙት የእንቅስቀሴ እና የእንቅልፍ እጦት ገጠመኞቹ ተናግሯል፡፡
ወደፊት ወደ ጠፈር መጓዝ የሚፈልጉ ጎብኚዎች ለአምስት ያህል ቀናት እንዲህ ዐይነቱን ነገር ሊለማመዱ እንደሚገባ ገልጿል፡፡
ማዔዛዋ ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት ጠፈር ላይ ምን ሊያደርግ እንደሚችል የተለያዩ ህዝባዊ አስተያየቶችን ሲያሰባስብ ነበር፡፡ ባድሜንተን እና ሌሎች ስፖርቶችን መጫወትን ጨምሮ አንድ መቶ ጉዳዮችንም ዘርዝሮ ጽፏል፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ቨርጂኒያ ያደረገው ‘ስፔስ አድቬንቸር’ ነው የቱጃሩን ጉዞ ያዘጋጀው፡፡ ‘ስፔስ አድቬንቸር’ ከፈረንጆቹ 2001 እስከ 2009 ሌሎች ሰባት ቱሪስቶችን ወደ ጠፈር ልኳል፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ሩሲያውያን የፊልም ባለሙያዎች በማዕከሉ ተመሳሳይ ቆይታን አድርገው ፊልም ቀርጸው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡