ቢሊዮን ዶላሮች የፈሰሱበት ግዙፉ የዓለማችን ቴሌስኮፕ ወደ ጠፈር መጠቀ
በሰው ዐቅም ሊታዩ የማይችሉ አካላትን ጭምር ለማየት ያስችላል የተባለለት “ጄምስ ዌብ” የህዋን እና የከዋክብትን አፈጣጠር ለማጥናት ይረዳል መባሉ ይታወሳል
“ጄምስ ዌብ” ይሰኛል የተባለለት ቴሌስኮፑ በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) ነው ወደ ጠፈር የመጠቀው
ወሳኝ ነው የተባለለትና ቢሊዮን ዶላሮች የፈሰሱበት ግዙፉ የዓለማችን ቴሌስኮፕ ወደ ጠፈር መጠቀ፡፡
የአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም (ናሳ) በፈረንጆቹ ዛሬ ቅዳሜ ታህሳስ 25 ቀን 2021 ወደ ጠፈር ያመጠቀው ግዙፍ ቴሌስኮፕ “ጄምስ ዌብ” (JWST) ይሰኛል፡፡
ከደቡባዊ አሜሪካ ሰሜን ምስራቃዊ ባህር ዳርቻ ከምትገኘው ፍሬንች ጉያና የመጠቀው “ጄምስ ዌብ” የህዋን እና የከዋክብትን አፈጣጠር ጨምሮ ህይወት ያለው አካል ይኖር እንደሆነ ጠፈርን ለማሰስ ይጠቅማል ተብሏል፡፡
የአፖሎ 11 አብራሪ የነበረው ጠፈርተኛው ማይክል ኮሊንስ በ90 ዓመቱ አረፈ
በጠፈር 10 ዓመታትን የሚቆየው ቴሌስኮፑ 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የወጣበት ሲሆን ወደታሰበለት የጠፈር ስፍራ ይደርስ ዘንድ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኪሎ ሜትሮችን ይጓዛልም ነው የተባለው፡፡
ይህ የጨረቃን ርቀት አራት እጥፍ ያህል የሚበልጥ ነው፡፡ ጉዞው በአንድ ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የሚጠበቅ ሲሆን ህዋን ማሰስ እስከሚጀምር አምስት ያህል ወራት ሊወስድበት እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን “ጄምስ ዌብ” ስለ ህዋ እና ስላለንበት ሁኔታ የተሻለ ግንዛቤን ለመያዝ ያስችለናል ሲሉ ከሰሞኑ ተናግረዋል፡፡
ከዋክብቶች እና አጠቃላይ ስርዓተ ከዋክብት ከ14 ቢሊዮን ዓመታት በፊት እንዴት እንደተፈጠሩ ለማወቅ ወሳኝ ነውም ነው ተቋሙ የሚለው፡፡
ናሳ በ1990ዎቹ መባቻ ሃብል የተሰኘ የምርምር ቴሌስኮፕ (HST) ወደ ጠፈር መላኩን የተቋሙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡