በእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ሳቢያ በጋዛ በአንድ ሰዓት ውስጥ በአማካኝ 3 ልጆች ጉዳት ይደርስባቸዋል ተባለ
በአጠቃላይ እስካሁን 192 ፍልስጤማውያን እና 10 እስራኤላውያን በግጭቱ ህይወታቸውን አጥተዋል
በግጭቱ የ60 ህጻናት ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም 58 ከፍልስጤም 2 ከእስራኤል ናቸው
የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ከተከሰተ ዛሬ ወደ ሁለተኛ ሳምንት ተሸጋግሯል፡፡ ግጭቱን ተከትሎም ሀማስ ከ3 ሺህ በላይ ሮኬቶችን ወደ እሰራኤል የተለያዩ ከተሞች ያስወነጨፈ ሲሆን ፣ እስራኤል በአጸፋው በተከታታይ በጋዛ ሰርጥ የአየር ድብደባዎችን እያካሄደች ነው።
ይህ የእስራኤል እና ሀማስ ግጭት ህጻናትን ሰለባ በማድረግ ላይ ነው፡፡ በጋዛ ብቻ በአንድ ሰዓት ውስጥ በአማካኝ ሶስት ህጻናት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ነው ዓለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት ያስታወቀው።
ግጨቱን ተከትሎም የ60 ህጻናት ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 58 ከፍልስጤም ፣ 2 ከእስራኤል መሆኑ ተነግሯል።
በጋዛ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በግጭቱ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 366ቱ ህጻናት መሆናቸውን ነው የህጻናት አድን ድርጅት ያስታወቀው።
በፍልስጤም የዓለም አቀፉ የህጻናት አድን ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ጄሰን ሊ “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በግጭቱ ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም ይዘው ወደ እርምጃ እንዲገቡ ምን ያክል ቤተሰቦች የሚወዱትን ልጆች ማጣት አለባቸው?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
“መኖሪያ ቤታቸው በተከታታይ በቦምብ በሚደበደብበት ሰዓት እነዚህ ህጻናት የት ሊደበቁ ይችላሉ?” የሚል ጥያቄም ያነሱት ዳይሬክተሩ “ስፍራው አሁን ላይ ለህጻናቱ ገሃነም ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የእስራኤል እና የሀማስን ግጭት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እያካሄደች ያለው የአየረ ድበበዳ ዛሬ ስምንተኛ ቀኑን ይዟል።
የእስራኤል አየር ኃይል በዛሬው እለት ጠዋት በጋዛ ሰርጥ እያካሄደ ያለውን የአየር ድብደባ የቀጠለ ሲሆን፣ ሀማስም ወደ እስራኤል የተለያዩ ከተሞች ሮኬቶችን ማስወንጨፉን እንደቀጠለ ነው።
የእስራኤል አየር ኃይል በትናትናው እለት በጋዛ ሰርጥ በፈጸመው የአየር ድብደባ የ42 ፍልስጤማውያን ህይወት ያለፈ ሲሆን፣ በርካቶች መቁሰላቸውም ተነግሯል።
እስካሁን 192 ፍልስጤማውያን እና 10 እስራኤላውያን በግጭቱ ህይወታቸውን አጥተዋል ፤ ከአንድ ሺ በላይ ሰዎችም ተጎድተዋል።
በርካታ ሀገራት በጋዛ እየተካሄደ ያለው ግጭት እንዳሳሰባቸው ያስታወቁ ሲሆን፤ ቻይና ደግሞ ግጭቱ እልባት እንዳያገን አሜሪካ እንቅፋት ሆናለች ስትል ወቅሳለች።