በእስራኤል የአየር ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 53 ደረሰ
ህይወታቸውን ካጡ ፍልስጤማውያን መካከል 14ቱ ህጻናት ፣ 3ቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው
ሀማስ ከጋዛ ሰርጥ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈ ሲሆን 6 እስራኤላውያን ተገድለዋል
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እየፈፀመች ባለው የአየር ጥቃት ህይወታቸው ያለፈ ፍልስጤማውያን ቁጥር 53 መድረሱን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በአየር ድብደባው ህይወታቸው ካለፈ ፍልስጤማውያን መካከል 14ቱ ህጻናት ሲሆኑ፤ 3ቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል።
ህይወታቸውን ካጡት በተጨማሪ ከ300 በላይ ሰዎች በድበደባው መቁሰላቸውንም ነው ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት ያስታወቀው።
ከእስራኤል በኩል የ6 ሰዎች ህይወት በሀማስ ጥቃት ማለፉ ተነግሯል።
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የአየር ድብደባ መፈጸም የጀመረችው ፣ በኢየሩሳሌም የነገሰውን ውጥረት እና ግጭት ተከትሎ የሀማስ ኃይሎች ወደ እስራኤል ሮኬት ተኩሰዋል በሚል ነው።
የእስራኤል ጦር እንዳስታወቀው ሀማስ ከጋዛ ሰርጥ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሮኬቶችን ወደ ተለያዩ የእስራኤል ክፍሎች ተኩሷል።
እስራኤል በበኩሏ በጋዛ ሰርጥ በሁለት ቀናት ውስጥ 500 ኢላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች፡፡
በአየር ድብደባውም 15 የሀማስ ታጣቂ ኃይሎችን ገድያለሁ ማለቷ ነው የተነገረው።
የኢየሩሳሌሙ ግጭት ባሳለፍነው ሰኞ በእየሩሳሌም በሚገኘው የሙስሊሞች ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ በሆነው አል አቅሳ መስጂድ ጊቢ ውስጥ እና በዙሪያው መከሰቱ ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በትናትናው እለት አስቸኳይ ስበሰባ የተቀመጠ ሲሆን፤ የተመድ ዋና ጸኃፊን ጨምሮ የዓለም ሀገራት መሪዎች ሁኔታው እንዳሳሰባቸው እና ሁሉም ኃይሎች ሁኔታውን እንዲያረግቡት ጠይቀዋል።