የሀማስ ከፍተኛ አመራር መገደሉን ተከትሎ በርካታ ሮኬቶች ወደ እስራኤል መወንጨፋቸው ተነገረ
በጋዛ የሚገኙ የሀማስ ሚሊሺያዎች ምሽቱን 130 ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ማስወንጨፋቸውን አስታውቀዋል
ጠ/ሚ ኔታንያሁ የፖሊስ ሀይሉን ለማገዝ የሀገሪቱን ጦር እንደሚያሰማሩ ገልጸዋል
እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው የአየር ድብደባ ከፍተኛ የሀማስ ሚሊሺያ መሪን መግደሏን ተከትሎ ሀማስ በቁጥር በርከት ያሉ ሮኬቶችን ማስወንጨፉ ተነግሯል።
በጋዛ የሚገኙ የሀማስ ሚሊሺያዎች እንዳስታወቁት፣ በእስራኤል የአየር ድብደባ በጋዛ ከተማ የሚገኘው አል ሸሩክ ህንጻ መደርመሱን ተከትሎ 130 ሮኬቶች ወደ እስራኤል ተተኩሰዋል።
በእስራኤል ድብደባ የፈረሰው ህንጻ በከተማው ሶሶተኛው ረጅሙ ህንጻ ሲሆን፤ አል አቅሳ የተባለ እና በሀማስ የሚተዳደር የቴሌቪዥን ጣቢያ የሚገኝበት ነበር።
እስራኤል በአየር ድብደባው የሀማስ ከፍተኛ መሪን መግደሏን እና የሀማስ የሚሳኤል ማስወንጨፊያ ጣቢያዎችን ኢላማ ያደረገ ድበደባ መፈጸሟን አስታውቃለች።
ሀማስም በድበደባው ከፍተኛ የቡድኑ አዛዥ እና ሌሎችም መሪዎቹ እንደሞቱበት አረጋግጧል።
የእስራኤል መከላከያ ሀይል በትናትናው እለት ባወጣው መግለጫ በጋዛ ሰረጥ የፈጸመው ጥቃት እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ከተከሰተው ግጭት ወዲህ ከፍተኛው ነው ብሏል።
በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች ከአየር ድበደባው ቀደም ብሎ ህንጻዎችን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ፣ በጋዛ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ግን በርካታ ንጹሃን ዜጎች እየሞቱ ነው ብለዋል።
ኤ.ኤፍ.ፒ እንደዘገበው ባሳለፍነው ማክሰኞ በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላት በእስራኤል አየር ድብደባ ህይወታቸው አልፏል።
በኢየሩሳሌም ከነበረው ከፍተኛ ውጥረት ጋር በተያያዘ ግጭቱ ባሳለፍነው ሰኞ የተጀመረ ሲሆን፤ እስካሁን 69 ፍልስጤማውያን እና 7 እስራኤላውያን በግጭቱ ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉም ተነግሯል።
በግጭቱ ህወታቸው ካለፈ ንጹሀን ውስጥ 17 ህጻናት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከ390 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ነው የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር መረጃ የሚያመልክተው።
የእስራኤል ፖሊስ በበኩሉ 374 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና 36 የፖሊስ አባላት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ህግና ስርዓትን የማስጠበቅ ስራው ላይ የፖሊስ ሀይሉን ለማገዝ የሀገሪቱን ጦር እንደሚያሰማሩ ገልጸዋል።
የእስራኤል መንግስት የዜጎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ ያለውን ሀይል በሙሉ ይጠቀማል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት በበኩላቸው እስራኤል እያካሄደች ያለውን ወታደራዊ እርምጃ እንደሚያወግዙ በትዊተር ገጻቸው በሚያወጧቸው መረጃዎች አስታውቀዋል።
ባሳለፍነው ሰኞ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋል ሀማስ ከ1 ሺህ 500 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ያስወነጨፈ ሲሆን፤ እስራኤልም ከ500 በላይ በሚሆኑ የሀማስ ኢላማዋዎች ላይ የአየር ድብደባ ፈጽማለች።