በእስራኤል የአየር ጥቃት የ24 ፍልስጤማውያን ህይወት አለፈ
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የአየር ድብደባ የፈጸመችው የሀማስ ሀይሎች ወደ እስራኤል ሮኬት መተኮሳቸውን ተከትሎ ነው
ግጭቱ በትናትናው እለት የተጀመረ ሲሆን፤ ከ300 በላይ ፍልስጤማውያን ጉዳት ደርሶባቸዋል
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፈፀመችው የአየር ጥቃት የ24 ፍልስጤማውያን ህይወት ማለፉን የፊሊስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል የአየር ድብደባውን የፈጸመችው የሀማስ ሀይሎች ወደ እስራኤል ሮኬት መተኮሳቸውን ተከትሎ እንደሆነም ተነግሯል።
በአየር ድብደባውም 9 ህጻናትን ጨምሮ የ24 ሰዎች ህይወት ማለፉን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል በበኩሏ በጋዛ ሰርጥ በ139 የሀማስ ታጣቂዎች ኢላማ ላይ የአየር ድብደባ መፈጸሟን በዛሬው እለት አስታውቃለች።
በአየር ድብደባውም 15 የሀማስ ታጣቂ ሀይሎችን ገድያለሁ ማለቷ ነው የተነገረው።
የእየሩሳሌሙ ግጭት በትናንትናው እለት በእየሩሳሌም በሚገኘው የሙስሊሞች ሦስተኛው ቅዱስ ስፍራ በሆነው አል አቅሳ መስጂድ ጊቢ ውስጥ እና በዙሪያው መከሰቱ ይታወሳል።
የእስራኤል ፖሊሶች ድንጋይ በሚወረውሩባቸው የተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የፕላስቲክ ጥይቶችን እና አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ እንዲሁም ውሃ በመጠቀሙ በወሰዱት እርምጃ ከ300 በላይ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በትናትናው እለት አስቸኳይ ስበሰባ የተቀመጠ ሲሆን፤ የተመድ ዋና ጸኃፊን ጨምሮ የዓለም ሀገራት መሪዎች ሁኔታው እንዳሳሰባቸው እና ሁሉም ሀይሎች ሁኔታውን እንዲያረግቡት ጠይቀዋል።