እስራኤል ዛሬ ባካሄደችው የአየር ድብደባ ብቻ ቢያንስ የ37 ፍልስጤማውያን ህይወት አልፏል
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ እያካሄደች ያለውን የአየረ ድበበዳ ዛሬ ለሰባተኛ ቀን ቀጥላለች
ከሀማስ በኩል እስከአሁን ድረስ ከ3 ሺ በላይ ሮኬቶች ወደ እስራኤል የተለያዩ ከተሞች ተወንጭፈዋል
በዛሬው የአየር ድበደባ ብቻ ቢያንስ የ37 ፍልስጤማውያን ህይወት ማለፉን እና ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች ውስጥ 13 ህጻናት መሆናቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሎም በእራኤል የአየር ድብደባ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 185 የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ 52 ህጻናት መሆናቸው ነው የተነገረው።
ሀማስ በበኩሉ ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ከ3 ሺ በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል የተለያዩ ከተሞች አስወንጭፏል።
እስራኤል በዛሬው እለት እያደረገች ስላለው የአየር ድብደባ መረጃ ከመስጠት የተቆጠበች ቢሆንም ፣ በዛሬው ጥቃት አንድ ከፍተኛ የሀማስ አመራር ቤትን ማውደሟን ከስፍራው የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡
በጋዛ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች በበኩላቸው በአየር ድበደባው ቆስለው ወደ ሆስፒታል የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መሆኑን አና ከሆስፒታሎች አቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን አስታውቀዋል።
የጋዛ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በህንጻዎች ፍርስራሽ ስር የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ለማውጣት እየሰሩ እንደሚገኙ ነው የተነገረው።
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ፣ እሰራኤል በፍልስጤማውያን ላይ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት እየፈጸመች መሆኑን በመግለጽ ፣ በጋዛ እየተካሄደ ያለው አስከፊ ኦፕሬሽን በአፋጣን እንዲቆም ዓለም አቀፉ ማሀበረሰብ በጋራ እንዲንቀሳቀስ ጥሪ አቅርቧል።
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ላይ ስብሰባ እንደሚቀመጥ የሚጠበቅ ሲሆን፤ 57 አባላት ያለው ኢስላሚክ ኮርፖሬሽን ድርጅት ደግሞ በጉዳዩ ላይ በቨርቹዋል አስቸኳይ ስብሰባ ማድረግ ጀምሯል።