በመስከረም 20ው ምርጫ ለ47 የተወካዮች ም/ቤት መቀመጫ ምርጫ ይካሄዳል
22 ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሳተፉበት ምርጫ ከ7 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ድምፅ እንደሚሰጥም ቦርዱ አስታውቋል
10 በሚደርሱ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከፀጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ መስከረም 20 ምርጫው አይካሄድም
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚከናወነው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።
ቦርዱ በመግለጫው፤ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝበውሳኔን ያካተተው ጠቅላላ ምርጫ ከ10 ቀናት በኋላ እንደሚካሄድ አስታውቋል።
ቦርዱ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳል ብሏል።
ለዚህ ቀኑን ከመወሰን አንስቶ እያንዳንዱን ስራ የሚያሳይ የጊዜ ሰሌዳ ተዘጋጅቶ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሁለት ውይይት መደረጉን ነው የገለፀው።
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶልያና ሽመልስ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱን ከተመለከቱ ዝግጅቶች ጋር በተያያዘ መግለጫ ሰጥተዋል።
እንደ መግለጫው መስከረም 20 ቀን የሚካሄደው ምርጫ በአጠቃላይ በሐረር፣ በደቡብ በህርብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በሶማሌ ክልል ለተወካዮች ምክር ቤት 47 ለክልል ምክር ቤት 105 ምርጫ ክልሎች ላይ ይከናወናል።
በእለቱ 7 ሺ 54 ምርጫ ጣቢያዎች ድምጽ አሰጣጡ እንደሚዘጋጁ የገለጸው ቦርዱ፤ 30 ሺህ የሚጠጉ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምርጫውን ያስፈፅማሉ ብለዋል።
ምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች የክለሳ ስልጠና እና ለምርጫ አስፈጻሚዎች ደግሞ የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ ( ምዝገባ በሚደረግባቸው ቦታዎች) እና ድምጽ መስጫ ቀንን እንዲሁም የህዝበ ውሳኔ አፈጻጸምን አስልክቶ ስልጠናዎች ወስደዋል።
በስልጠናው በአጠቃላይ 26 ሺህ በላይ አስፈጻሚዎች ተሳትፈዋል እንደ ኮሙኒኬሽን አማካሪዋ ገለጻ።
በጠቅላላ ምርጫው የሚወዳደሩት 22 የፓለቲካ ፖርቲዎች እጩዎችን አቅርበዋል።
ከመስከረም 8 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምረን የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶችን ወደ ጣቢያዎች እያጓጓዙ መሆኑን የገለጹት ሶልያና እስከ ነገ ወዲያ መስከረም 12 ድረስ እንጨርሳለን ብለዋል።
በጠቅላላ ምርጫው እና ህዝበ ውሳኔው ድምጽ የሚሰጡ ዜጎች ቁጥር 7 ነጥብ 6 ሚልዮን መሆኑንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በድሬዳዋ ሁለት ምርጫ ጣቢያዎች የሚሰጠው ድምፅ ቦርዱ ከአሁን ቀደም እንዲደገም በወሰነው ውሳኔ መሠረት የሚካሄድ መሆኑን የገለፁት አማካሪዋ ምርጫው እንዲደገም የተወሰነበት የቀጫ ምርጫ ክልል አሁንም የደህንነት ስጋት ያለበት መሆኑን ተከትሎ ልዩ ውሳኔ የሚያስፈልገው ነው ብለዋል።
አጣዬና መሠል የሰሜን ሸዋ አካባቢዎችን ጨምሮ 10 በሚደርሱ የአማራ ክልል አካባቢዎች ከጸጥታ ችግሮች ጋር በተያያዘ የመራጮች ምዝገባ አለመፈጸሙን ተከትሎ መስከረም 20 ድምፅ እንደማይሰጥ አስታውቀዋል።
በሰኔ 14 በተካሄድው ጠቅላላ ምርጫ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ፣ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል ድምጽ ማግኘቱን ቦርዱ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትም መስከረም 24 አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት አሳውቆ ነበር።