በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የተጀመረው ጥረት የት ደረሰ?
በዓለማችን ለሰራተኞቻቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ካላቸው አምስት አገራት መካከል ሶስቱ በአፍሪካ ይገኛሉ
ውሳኔው በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚጸድቅ ከሆነ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ ይቋቋማል ተብሏል
የዓለም የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የአፍሪካ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ፎረም በጥር ወር 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባካሄደው የሁለት ቀናት ጉባኤ ላይ የአፍሪካ አገራት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወስኑ የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሃፊ ሻረን ባሮው አሳስበው ነበር፡፡
ዋና ጸሃፊው በወቅቱ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወስኑ ካሳሰቧቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ቀሪዎቹ ሀገራት ደግሞ ጋና፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋልና ዛምቢያ ነበሩ፡፡
በዚህ ማሳሰቢያ መሰረትም ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለልን ለመወሰን ረቂቅ ህግ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ገልጾም ነበር፡፡
በመሆኑም አል ዐይን አማርኛ ጉዳዩ የት ደረሰ ሲል የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ኢሰማኮን ጠይቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ11 ዓመት በፊት የፈረመችውን የቤት ሰራተኞች መብት ህግ እንድታጸድቅ ተጠየቀች
የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለአል ዐይን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን ስለተጀመረው ስራ አብራርተዋል፡፡
ኮንፌዴሬሽኑ በ2013 ዓ/ም በወቅቱ የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ከሚባለው ተቋም ጋር ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የሚረዳ ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን ያብራሩት አቶ ካሳሁን ህጉ በሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ በተስማማነው መሰረት ረቂቅ ህጉ ለሚኒስትሮች ምክር ቤትም ቀርቧል ብለዋል፡፡
ይሁንና ወቅቱ አገር አቀፍ ምርጫ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ረቂቅ ህጉ በወቅቱ በነበረው መንግስት ሳይታይ ቀርቷል፣ በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣው አዲሱ መንግስትም በቶሎ ረቂቅ ህጉ ላይ ተወያይቶ ደንቦችን ያጸድቃል ብለን ብንጠብቅም እስካሁን ረቂቅ ህጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት አልታየም፡፡
በመሆኑም ምክር ቤቱ በረቂቅ ህጉ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ከስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ግፊት በማድረግ ላይ እንደሆኑ አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ ህጉ ላይ ተወያይቶ ዉሳኔ ካሳለፈ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ ላይ በተቀመጠው መሰረት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ ይቋቋማልም ነው ያሉት፡፡
ቦርዱ ከአሰሪ፣ ከሰራተኛ እና ከመንግስት የተውጣጣ አባላት የሚኖሩት ሲሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ ድርድር እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
አሁን ባለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ዝቅተኛው የተቀጣሪ ደመወዝ ለጊዜው 6 ሺህ 800 ብር መሆን አለበት- የምጣኔ ሀብት ባለሙያ
የቦርዱ ድርድር አንድ ሰው በቀን ስንት ብር ቢከፈለው በልቶ ማደር ይችላል፣ በወርስ ስንት ይከፈል? በሚል በጥናት ላይ ተመስርቶ ውይይት እና ድርድር ከተደረገ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚወሰን እና ወደ ተግባር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በዓለማችን ለሰራተኞቻቸው ዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ ካላቸው አምስት አገራት መካከል ሶስቱ በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን ሞሪታኒያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ኢትዮጵያ ደግሞ አነስተኛ የሰራተኞች ክፍያ የሚፈጸምባቸው አገራት መሆናቸውን የዓlም ስራ ድርጅት መረጃ ያስረዳል፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና ጃፓን ደግሞ ለሰራተኞቻቸው በአንጻራዊነት የተሻለ ክፍያ የሚፈጽሙ አገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡