ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ከ1924 እስከ 2013 ዓ.ም
በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ በሴማዊ ቋንቋ ጥናት፣ በአማርኛ ግዕዝ ሥነ-ጹሑፍ እና ሰዋሰው በመምህርነት አግልግለዋል
ከ30 በላይ የጥናትና የምርምር መፅሀፍትን ለህትመት አብቅተዋል
አንጋፋው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ከ1950 እስከ 1960ዎቹ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሴማዊ ቋንቋ ጥናት፣ በአማርኛ ግዕዝ ሥነ-ጹሑፍ እና ሰዋሰው በመምህርነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በሀገራዊ ጉዳዮች በሚሰጡትም በሳል ሀሳቦች እና ትችቶችም በሕዝብ ዘንድ ይታወቃሉ።
የኢትዮጵያ ጥንታዊ መፃህፍትና መዛግብት በብዛት የተረጎሙ በጥልቀት የመረመሩ፣ በስፋት ያስተማሩ እንዲሁም ለትውልድ ያሻገሩ ምሁር ናቸው።
ከ30 በላይ የጥናትና የምርምር መፅሀፍት ያሳተሙት ፕሮፌሰር ጌታቸው፤ በበርካታ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም መጣጥፍ ያበረከቱ መሆናቸውም ይታወቃል።
ከዚህ በተጨማሪም በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቋንቋ የሚናገሩ ፤ የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር (ባህረ ሀሳብ) በዘመናዊ መልክ ተንትነው ያቀረቡና ያተሙ ሙሁር ናቸው።
የእውቁ የማካርተር ፋውንዴሽን ተሸላሚ የነበሩት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፤ የብሪቲሽ አካዳሚ የመጀመሪያ አፍሪካዊ አባልም ናቸው።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በርካታ ጥናታዊ ጽሁፎችን በአለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ከማሳተማቸውም ባሻገር በርካታ መጻህፍት ጽፈዋል።
ከእነዚህም መካከል-
ስለ ግዕዝ ስነ ጽሁፎች የተሰበሰቡ አንዳንድ ማስታወሻዎች
ደቂቀ እስጢፋኖስ፤ '' በህግ አምላክ'' ትርጉም
አንድ አፍታ ላውጋችሁ፤ በግል ህይወታቸው ካጋጠማቸው እና የደረሰባቸውን የጻፉበት
ባሕረ ሐሳብ፤ የኢትዮጵያ ዘመን ቆጠራ ቅርስን ከታሪክ ማስታወሻ ጋር
የአባ ባሕርይ ድርሰቶች ይገኙበታል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በ90 ዓመት እድሜያቸው የረጅም ዘመን የስደት ሂወት በመሩበት ዩናይትድ ስቴትስ ኒውዮርክ ህይወታቸው ማለፉም ተሰምቷል።