ፓርኮች እና ደኖች “በግድየለሽነት” እየተቃጠሉ መሆኑን የቱሪዝም ጋዜጠኞች ገለጹ
ለመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የእሳት ቃጠሎዎች መንስዔው ምንድነው?
በአርሲ ፣ በምስራቅ ሀረርጌ እና በሰሜን ሸዋ በሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የተነሳውን እሳት እስካሁን መቆጣጠር አልተቻለም
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ፓርኮች እና ደኖች ላይ እየተነሳ ያለው የእሳት አደጋ በግድየለሽነት፣ በቅድመ ዝግጅት ማነስና በግንዛቤ ችግር መሆኑን የኢትጵያ የቱሪዝም ጋዜጠኞች አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ጊዜ ወዲህ በየቦታው የእሳት አደጋ ተከሰተ የሚል ዜና መበራከቱን ተከትሎ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት ጋዜጠኞቹ ፣ አሁንም በቀሪ የበጋ ጊዜያት ከፍተኛ ቅድመ ጥንቃቄ ካልተደረገ ከዚህ የከፋ ችግር ሊኖር እንደሚችል አሳስበዋል፡፡
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ በባህል እና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰራው ሔኖክ ስዩም (ተጓዡ ጋዜጠኛ) ፣ ሕብረተሰቡ የእሳት አደጋ ቢነሳ ምን መደረግ አለበት የሚለውን ቀድሞ መጠየቅና የአካባቢውን ሀብቶች እንደራሱ ማየት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ እንደ ሀገር የተፈጥሮ ሀብቱ በእሳት የሚደርስበትን ውድመትና ጫና ለመቀነስ፣ የእሳት መከላከያ ስትራቴጅ እንደሚያስፈልግም ነው ሔኖክ ያነሳው፡፡ አሁንም ቀሪዎቹ የበጋው ቀናት የሙቀቱ መጠን የሚከርበት በመሆኑ በደን እና በብሔራዊ ፓርኮች ድንበር ላይ የሚኖሩ ዜጎች የእርሻ ቦታን ለማጽዳት ፤ የሚለኩሱት እሳት ችግር እንዳይፈጥር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ጋዜጠኛው አሳስቧል፡፡በመሆኑም እስከ ቀበሌ ድረስ ባሉ የግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት ጠንካራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፣ የክትትልና ድጋፍ ስራ መሰራት እንዳለበትም ነው የገለጸው።
በተለያየ ምክንያት ቃጠሎ የሚደርስባቸውን የተፈጥሮ ሀብቶች ለመጠበቅ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የጥበቃ ባለሙያዎች በተጨማሪ የሀገሪቱ የጸጥታ ሀይሎች እውቀቱ ፣ ግንዛቤውና ዝግጅቱ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚገባም ጋዜጠኛ ሔኖክ አክሏል።
ሌላኛው የቱሪዝም እና ባሕል ጋዜጠኛ ምኒሊክ ፋንታሁን ፣ ኢትዮጵያ ብዙ ሀብቶች (ፓርኮች) ቢኖሯትም ሀብቷን ከእሳት ቃጠሎ እና ሌሎች ሰው ሰራሽ አደጋዎች መጠበቅ የሚያስችል አቅም እንደሌላት አንስቷል፡፡ ቀድሞ ዝግጅት ቢደረግ ኖሮ “የወደሙብንን ፓርኮች ማዳን ይቻል ነበር” ያለው ምኒሊክ ፣ በበጋ ወቅት እሳት መነሳቱ የተለመደ መሆኑን በመጥቀስ ፣ ለቀጣይ ወቅቶች አስቀድሞ መዘጋጀት እንደሚገባ ጠቁሟል። ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ውስጥ 8 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው በፓርኮችና ጥብቅ ቦታዎች የተሸፈነ ቢሆንም ለዚህ ሀብት ጥበቃ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንም ነው ጋዜጠኛ ምኒሊክ የገለጸው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ብሔራዊ ሀብቶችን ከመሰል ውድመት ለመጠበቅ የሚያስችል አቅም መገንባት እንደሚገባ አንስቷል፡፡
የእሳት ቃጠሎ ወፍ ዋሻ የተፈጥሮ ጥብቅ ደን
ከቀናት በፊት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ የእሳት አደጋ ተነስቶ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጭላሎ ተራራ፣ በምስራቅ ሀረርጌ በሚገኘው አሰቦት ገዳም እና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኘው ወፍዋሻ ጥብቅ ደን ላይ ተከሰተ የተባለው እሳት አደጋ እስካሁን አልጠፋም ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናቃቸው ብርሌው ፣ በሀገሪቱ በተለያዩ ፓርኮችና የዱር እንስሳት መጠለያ ቦታዎች ላይ እየደረሰ ላለው የእሳት አደጋ ምክንያቱ የደን መጨፍጨፍ፣ ልቅ ግጦሽ ፣ ሕገ ወጥ ከሰል ማክሰልና የመሳሰሉት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ አሁን ላይ እሳቱን ለማጥፋት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት የማከናወን እንዲሁም የሚመለከታቸውን አካላትና ተቋማት ማሳተፍ ላይ ትኩረት ማድረጉንም አቶ ናቃቸው አንስተዋል፡፡
በቀጣይ በብሔራዊ ፓርኮች ላይ መሠረተ ልማቶችንና ግብዓቶችን ማሟላትም ትኩረት እንደሚደረግበት ያዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ የእሳት አደጋዎች ፣ ጋዜጠኞች እና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከቸልተኝነት እና ከግለሰቦች የግል ጥቅም ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን ያስቀምጡ እንጂ ፖለቲካዊ ትርጓሜ የሚሰጡ አካላትም አሉ፡፡ ከፓርኮች እና ደኖች ባለፈ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይም ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ዜናዎችን መስማት አሁን አሁን እየተለመደ መጥቷል፡፡