በኮሮና ተጠርጥሮ ወደ ማቆያ እየተወሰደ ሳለ አምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠ ግለሰብ ተያዘ
በኮሮና ተጠርጥሮ ወደ ማቆያ እየተወሰደ ሳለ አምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠ ግለሰብ ተያዘ
በኮሮና ቫይረስ ተጠርጥሮ ወደ ማቆያ ቦታ በመውሰድ ላይ ሳለ አምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠው ግለሰብ በፌዴራልና በለጋምቦ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት እንዲሁም በፀጥታ ሃይሎች ትብብር በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ፡፡
ግለሰቡ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ 07 ቀበሌ ሰላም በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ሲሆን ከአንድ ወር በፊት በባህር ከሀገር ውጭ የወጣና አሁንም በባህር የተመለሰ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የለጋምቦ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት አበባው እንደገለጹት በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ከውጭ ሀገር ተመልሶ አዲስ አበባ ሲደርስ የበሽታው ምልክቶች ታይተውበት ወደ ምርምራ በመወሰድ ላይ እያለ አምቡላንስ ሰብሮ ያመለጠ ነው፡፡
ግለሰቡ ከፌዴራል በመጣው ቡድን አማካኝነት ወደ ማቆያ ቦታው ይወሰዳል ተብሏል፡፡
ተጠርጣሪው ግለሰብ በትናንትናው እለት ደሴ ከተማ ያደረ ሲሆን ዛሬ መጋቢት 06 ቀን 2012 ዓ.ም ጧት በሳይንት አጅባር አገር አቋራጭ አውቶቡስ ተሳፍሮ ገነቴ ከተማ ለመድረስ ከአራት ኪሎ ሜትር ያልበለጠ ጉዞ ሲቀረው ወለቃ ወንዝ ላይ በተደረገ ፍተሻ በቁጥጥር ስር መዋሉን አቶ ጌትነት አስረድተዋል፡፡
ግለሰቡ ተጠርጣሪና በበሽታው መያዙ ገና ያልተረጋገጠ መሆኑን ፣ብሎም አካባቢው ገብቶ ሳይሰወር በቁጥጥር ስር መዋሉን በመረዳት ህብረተሰቡ ተረጋግቶ ራሱን እንዲጠብቅ ሲሉ ኃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ምንጭ፦ ለጋምቦ ወረዳ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት